ሮሜ 2:2-11 - ሁሉንም ስሪቶች ያወዳድሩ

ሮሜ 2:2-11 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)

እንደዚህ በሚያደርጉትም ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነተኛ መሆኑን እናውቃለን። እንግዲህ አንተ ሰው በሌሎች ላይ እየፈረድህ ያንኑ የምታደርግ ከሆነ፣ ከእግዚአብሔር ፍርድ የምታመልጥ ይመስልሃል? ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሓ የሚመራህ መሆኑን ሳትገነዘብ፣ የቸርነቱን፣ የቻይነቱንና የትዕግሥቱን ባለጠግነት ትንቃለህ? ነገር ግን በድንዳኔህና ንስሓ በማይገባ ልብህ ምክንያት ትክክለኛ ፍርዱ ሲገለጥ በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን በራስህ ላይ ቍጣን ታከማቻለህ። እግዚአብሔር “ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ይሰጠዋል”። በጎ የሆነውን ጸንቶ በማድረግ ክብርን፣ ሞገስንና ዘላለማዊነትን ለሚሹ የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸዋል። ነገር ግን በራስ ወዳዶች፣ እውነትን ትተው ክፋትን በሚከተሉ ፍርድና ቍጣ ይደርስባቸዋል። ክፉ በሚያደርግ በማንኛውም ሰው፣ አስቀድሞ በአይሁድ ከዚያም በአሕዛብ ላይ መከራና ጭንቀት ይሆናል፤ ነገር ግን በጎ ለሚሠራ ለማንኛውም፣ አስቀድሞ ለአይሁድ ከዚያም ለአሕዛብ ክብር፣ ሞገስና ሰላም ይሆንለታል፤ እግዚአብሔር ለማንም አያደላምና።

ያጋሩ
ሮሜ 2 NASV

ሮሜ 2:2-11 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)

ይህን በሚያደርጉ ሰዎች ላይ፥ እግዚአብሔር የሚገባቸውን እንደሚፈርድባቸው እናውቃለን። አንተ ሰው! እንዲህ በሚያደርጉት ሰዎች ላይ እየፈረድክ፥ እነርሱ የሚያደርጉትን ስታደርግ ከእግዚአብሔር ፍርድ የምታመልጥ ይመስልሃልን? ወይስ የእግዚአብሔርን የደግነቱንና የቻይነቱን፥ የታጋሽነቱንም ብዛት ትንቃለህን? እግዚአብሔር ደግነቱን ያበዛልህ አንተን ወደ ንስሓ ለመምራት እንደ ሆነ አታውቅምን? እንግዲህ አንተ ንስሓ ባለመግባትህና እልኸኛ በመሆንህ የእግዚአብሔር ቊጣና ትክክለኛ ፍርድ በሚገለጥበት ቀን ቅጣትህ እንዲበዛ ታደርጋለህ። እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ እንደየሥራው ይሰጠዋል። በመልካም ሥራ በመጽናት ምስጋናና ክብርን የማይጠፋ ሕይወትንም ለሚፈልጉ እግዚአብሔር የዘለዓለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል። የራሳቸውን ጥቅም በሚፈልጉ፥ ለእውነት በማይታዘዙና ለዐመፅ በሚታዘዙ ዐድመኞች ላይ ግን የእግዚአብሔር ቊጣና መቅሠፍት ይመጣባቸዋል። በመጀመሪያ በአይሁድ፥ ቀጥሎም በአሕዛብ ክፋት በሚያደርጉ ሰዎች ሁሉ ላይ መከራና ጭንቀት ይመጣባቸዋል። ነገር ግን መልካም ነገርን ለሚያደርጉ ሰዎች ሁሉ ለአይሁድም ሆነ ለአሕዛብ ምስጋናና ክብር ሰላምም ይሰጣቸዋል። እግዚአብሔር በሰዎች መካከል አያዳላም።

ሮሜ 2:2-11 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))

ይህም እን​ደ​ዚህ በሚ​ያ​ደ​ርጉ ሰዎች ላይ ቅጣት የሚ​ያ​መጣ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፍርዱ እው​ነት እንደ ሆነ እና​ው​ቃ​ለን። አንተ ሰው ሆይ፥ በሌላ ላይ አይ​ተህ የም​ት​ጠ​ላ​ው​ንና የም​ት​ነ​ቅ​ፈ​ውን ያን አንተ ራስህ የም​ት​ሠ​ራው ከሆነ፥ ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፍርድ እን​ደ​ም​ታ​መ​ልጥ ታስ​ባ​ለ​ህን? ወይስ በቸ​ር​ነቱ ብዛት በመ​ታ​ገሡ፥ ለአ​ን​ተም እሺ በማ​ለቱ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን አላ​ዋቂ ልታ​ደ​ር​ገው ታስ​ባ​ለ​ህን? የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርስ ቸር​ነቱ አን​ተን ወደ ንስሓ እን​ዲ​መ​ል​ስህ አታ​ው​ቅ​ምን? ነገር ግን ልቡ​ና​ህን እንደ ማጽ​ና​ትህ፥ ንስ​ሓም እንደ አለ​መ​ግ​ባ​ትህ መጠን የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እው​ነ​ተና ፍርድ በሚ​ገ​ለ​ጥ​በት ቀን መቅ​ሠ​ፍ​ትን ለራ​ስህ ታከ​ማ​ቻ​ለህ። እርሱ በእ​ው​ነ​ተና ፍርዱ ለሁሉ እንደ ሥራው ይከ​ፍ​ለ​ዋ​ልና። በበጎ ምግ​ባር ጸን​ተው ለሚ​ታ​ገሡ፥ ምስ​ጋ​ናና ክብ​ርን፥ የማ​ይ​ጠፋ ሕይ​ወ​ት​ንም ለሚሹ እርሱ የዘ​ለ​ዓ​ለም ሕይ​ወ​ትን ይሰ​ጣ​ቸ​ዋል። ለሚ​ክ​ዱና እው​ነ​ትን ለሚ​ለ​ውጡ፥ ዐመ​ፅ​ንም ለሚ​ወ​ድዱ ሰዎች ዋጋ​ቸው ቍጣና መቅ​ሠ​ፍት ነው። መከ​ራና ጭን​ቀት አስ​ቀ​ድሞ በአ​ይ​ሁ​ዳዊ፥ ደግ​ሞም በአ​ረ​ማዊ፥ ሥራዉ ክፉ በሆነ ሰው ሁሉ ላይ ነው። ምስ​ጋ​ናና ክብር፥ ሰላ​ምም አስ​ቀ​ድሞ ለአ​ይ​ሁ​ዳዊ፥ ደግ​ሞም ለአ​ረ​ማዊ፥ ሥራዉ መል​ካም ለሆነ ሁሉ ነው። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ለሰው ፊት አያ​ዳ​ላ​ምና።

ሮሜ 2:2-11 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))

እንደዚህም በሚያደርጉት ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነተኛ እንደ ሆነ እናውቃለን። አንተም እንደዚህ በሚያደርጉ የምትፈርድ ያንም የምታደርግ ሰው ሆይ፥ አንተ ከእግዚአብሔር ፍርድ የምታመልጥ ይመስልሃልን? ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን? ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ። እርሱ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ያስረክበዋል፤ በበጎ ሥራ በመጽናት ምስጋናንና ክብርን የማይጠፋንም ሕይወት ለሚፈልጉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል፤ ለዓመፃ በሚታዘዙ እንጂ ለእውነት በማይታዘዙትና በአድመኞች ላይ ግን ቍጣና መቅሠፍት ይሆንባቸዋል። ክፉውን በሚያደርግ ሰው ነፍስ ሁሉ መከራና ጭንቀት ይሆንበታል፥ አስቀድሞ በአይሁዳዊ ደግሞም በግሪክ ሰው፤ ነገር ግን በጎ ሥራ ለሚያደርጉ ሁሉ ምስጋናና ክብር ሰላምም ይሆንላቸዋል፥ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው። እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያዳላምና።

ሮሜ 2:2-11 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))

እንደዚህ በሚያደርጉት ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነተኛ እንደሆነ እናውቃለን። አንተም እንደዚህ በሚያደርጉ ላይ የምትፈርድ ያንንም የምታደርግ ሰው ሆይ! ከእግዚአብሔር ፍርድ የምታመልጥ ይመስልሃልን? ወይስ የቸርነቱን፥ የቻይነቱን፥ የታጋሽነቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን? የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሓ ሊመራህ እንደሆነ አታውቅምን? ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሓ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቁጣ ቀን በራስህ ላይ ቁጣን ታከማቻለህ። እርሱ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ይሰጠዋል፤ በመልካም ሥራ በመጽናት ምስጋናንና ክብርን የማይጠፋንም ሕይወት ለሚፈልጉ የዘለዓለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል፤ በራስ ወዳዶች፥ ለእውነት በማይታዘዙት ነገር ግን ለዐመፃ በሚታዘዙት ላይ ቁጣና መቅሠፍት ይመጣባቸዋል። ክፉ በሚያደርግ ሰው ሁሉ ላይ፥ አስቀድሞ በአይሁዳዊ ከዚያም በግሪካዊ መከራና ጭንቀት ይሆንበታል፤ ነገር ግን መልካምን ለሚሠራ ሁሉ አስቀድሞ አይሁዳዊ ከዚያም ግሪካዊ ምስጋና፥ ክብርና ሰላም ይሆንለታል። በእግዚአብሔር ዘንድ ማዳላት የለምና።