1 ቆሮንቶስ 3
3
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተከሠተ መለያየት
1ወንድሞች ሆይ፤ በክርስቶስ ገና ሕፃናት እንደ መሆናችሁ፣ እንደ ሥጋውያን እንጂ እንደ መንፈሳውያን ልናገራችሁ አልቻልሁም። 2ገና ስላልጠነከራችሁ ወተት እንጂ ጠንካራ ምግብ አልመገብኋችሁም፤ አሁንም ቢሆን ገና ናችሁ። 3አሁንም ሥጋውያን ናችሁ፤ በመካከላችሁ ቅናትና ክርክር አለ። ታዲያ፣ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደለምን? ተግባራችሁስ እንደ ማንኛውም ሰው ተግባር መሆኑ አይደለምን? 4ምክንያቱም አንዱ፣ “እኔ የጳውሎስ ነኝ”፣ ሌላው ደግሞ፣ “እኔ የአጵሎስ ነኝ” ቢል፣ ሥጋ ለባሽ ብቻ መሆናችሁ አይደለምን?
5ለመሆኑ አጵሎስ ምንድን ነው? ጳውሎስስ ምንድን ነው? ጌታ ለእያንዳንዳቸው በሰጣቸው መጠን የሚሠሩ አገልጋዮች ናቸው፤ እናንተም ወደ እምነት የመጣችሁት በእነርሱ አማካይነት ነው። 6እኔ ተከልሁ፤ አጵሎስ ውሃ አጠጣ፤ ያሳደገው ግን እግዚአብሔር ነው። 7ስለዚህ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ፣ የሚተክልም ሆነ ውሃ የሚያጠጣ ምንም አይደለም። 8የሚተክልም ሆነ የሚያጠጣ አንድ ናቸው፤ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን የራሱን ሽልማት ይቀበላል። 9እኛ የእግዚአብሔር የሆንን ዐብሮ ሠራተኞች ነንና፤ እናንተም የእግዚአብሔር ዕርሻ፣ የእግዚአብሔር ሕንጻ ናችሁ።
10ከእግዚአብሔር በተሰጠኝ ጸጋ መጠን፣ እንደ አንድ ብልኅ ግንበኛ መሠረትን ጣልሁ፤ ሌላውም በላዩ ላይ ይገነባል፤ ነገር ግን እያንዳንዱ እንዴት እንደሚገነባ መጠንቀቅ አለበት። 11ምክንያቱም አንድ ጊዜ ከተመሠረተው መሠረት በቀር ሌላ መሠረት መጣል የሚችል ማንም የለም፤ ይህም መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 12ማንም በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ወይም በብር፣ በከበረ ድንጋይ ወይም በዕንጨት፣ በሣር ወይም በአገዳ ቢያንጽ፣ 13ሥራው እንዴት እንደ ሆነ ይታያል፤ ምክንያቱም ያ ቀን ወደ ብርሃን ያመጣዋል። በእሳት ስለሚገለጥ እሳቱ የእያንዳንዱን ሰው ሥራ ምንነት ይፈትናል። 14ማንም የገነባው ሥራ ቢጸናለት ሽልማቱን ይቀበላል፤ 15ሥራው የተቃጠለበት ግን ሽልማት ይቀርበታል፤ እርሱ ራሱ ግን ይድናል፤ ይሁን እንጂ የሚድነው በእሳት ውስጥ በጭንቅ እንደሚያልፍ ሆኖ ነው።
16እናንተ ራሳችሁ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ፣ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውስጣችሁ እንደሚኖር አታውቁምን? 17ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፤ ያም ቤተ መቅደስ እናንተ ናችሁ።
18ማንም ራሱን አያታልል፤ ከእናንተ ማንም በዚህ ዓለም ጥበበኛ የሆነ ቢመስለው፣ ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ራሱን እንደ ሞኝ ይቍጠር። 19የዚህ ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነውና፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤ “እርሱ ጥበበኞችን በራሳቸው ተንኰል ይይዛቸዋል፤”#3፥19 ኢዮ 5፥13 20በሌላ ስፍራ ደግሞ፣ “ጌታ የጥበበኞች ሐሳብ ከንቱ እንደ ሆነ ያውቃል”#3፥20 መዝ 94፥11 ተብሎ ተጽፏል፤ 21እንግዲህ ማንም በሰው አይመካ። ሁሉ ነገር የእናንተ ነውና፤ 22ጳውሎስም ሆነ አጵሎስ ወይም ኬፋ#3፥22 ጴጥሮስ ማለት ነው።፣ ዓለምም ሆነ ሕይወት ወይም ሞት፣ አሁን ያለውም ሆነ ወደ ፊት የሚመጣው፣ ሁሉ የእናንተ ነው፤ 23እናንተም የክርስቶስ ናችሁ፤ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው።
Currently Selected:
1 ቆሮንቶስ 3: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.