1 ጴጥሮስ 1
1
1የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ጴጥሮስ፤
በጳንጦስ፣ በገላትያ፣ በቀጰዶቅያ፣ በእስያና በቢታንያ ተበትነው በመጻተኛነት ለሚኖሩ ለእግዚአብሔር ምርጦች፤ 2እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ ካወቃቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመታዘዝ በደሙ ለተረጩትና በመንፈስ አማካይነት ለተቀደሱት፤
ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።
ሕያው ስለ ሆነው ተስፋ ለእግዚአብሔር የቀረበ ምስጋና
3የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባትና አምላክ ይባረክ፤ እርሱ ከታላቅ ምሕረቱ የተነሣ በኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሣት ምክንያት ለሕያው ተስፋ በሚሆን አዲስ ልደት፣ 4እንዲሁም በሰማይ ለማይጠፋ፣ ለማይበላሽና ለማይለወጥ ርስት እንደ ገና ወለደን። 5እናንተም በመጨረሻው ዘመን ሊገለጥ የተዘጋጀው ድነት እስኪመጣ ድረስ በእምነት አማካይነት በእግዚአብሔር ኀይል ተጠብቃችኋል። 6አሁን በብዙ ዐይነት ፈተና ውስጥ ሆናችሁ ለጥቂት ጊዜ መከራን ብትቀበሉም እንኳ በዚህ እጅግ ደስ ይላችኋል። 7እነዚህ ነገሮች በእናንተ ላይ የደረሱት፣ በእሳት ተፈትኖ ቢጠራም፣ ጠፊ ከሆነው ወርቅ ይልቅ እጅግ የከበረው እምነታችሁ፣ እውነተኛ መሆኑ እንዲረጋገጥና ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ምስጋናን፣ ክብርንና ውዳሴን እንዲያስገኝላችሁ ነው። 8እርሱንም ሳታዩት ትወድዱታላችሁ፤ አሁን ባታዩትም በርሱ ታምናላችሁ፤ መግለጽ በማይቻልና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ብሏችኋል፤ 9የእምነታችሁን ፍጻሜ፣ እርሱም የነፍሳችሁን ድነት እየተቀበላችሁ ነውና።
10ለእናንተ ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ ድነት ተግተው በጥንቃቄ ይመረምሩ ነበር፤ 11በእነርሱ ውስጥ የነበረው የክርስቶስ መንፈስ ስለ ክርስቶስ መከራ እንዲሁም ከመከራው በኋላ ስለሚሆነው ክብር አስቀድሞ በመናገር ያመለከታቸው ጊዜ መቼና እንዴት እንደሚፈጸም ይመረምሩ ነበር። 12አሁን ከሰማይ በተላከ መንፈስ ቅዱስ ወንጌልን ያበሠሩላችሁ ሰዎች የነገሯችሁን ነገር ባወሩላችሁ ጊዜ፣ እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳላገለገሉ ተገለጠላቸው። መላእክትም እንኳ ሳይቀሩ እነዚህን ነገሮች ይመኛሉ።
በቅድስና መኖር
13ስለዚህ ልባችሁን አዘጋጁ፤ ራሳችሁንም ግዙ፤ ተስፋችሁን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ ለእናንተ በሚሰጠው ጸጋ ላይ ሙሉ በሙሉ አድርጉ። 14ታዛዦች ልጆች እንደ መሆናችሁ መጠን ቀድሞ ባለማወቅ ትኖሩበት የነበረውን ክፉ ምኞት አትከተሉ። 15ነገር ግን የጠራችሁ እርሱ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተም በኑሯችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ 16ምክንያቱም “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ”#1፥16 ዘሌ 11፥44-45፤ 19፥2 ተብሎ ተጽፏል።
17ለሰው ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደየሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ የምትጠሩት ከሆነ፣ በዚህ ምድር በእንግድነት ስትኖሩ በፍርሀት ኑሩ። 18ከቀድሞ አባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከንቱ ከሆነ ሕይወት የተዋጃችሁት በሚጠፋ ነገር፣ በብር ወይም በወርቅ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ፤ 19ነገር ግን እናንተ የተዋጃችሁት ነውርና እንከን እንደሌለበት በግ ደም፣ በክርስቶስ ክቡር ደም ነው። 20እርሱ አስቀድሞ የታወቀው ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ሲሆን፣ አሁን ግን በመጨረሻው ዘመን ስለ እናንተ ተገለጠ። 21በርሱም አማካይነት፣ ከሞት ባስነሣውና ክብርን በሰጠው በእግዚአብሔር ታምናላችሁ፤ ስለዚህ እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ላይ ነው።
22እንግዲህ ለእውነት በመታዘዝ ነፍሳችሁን ስላነጻችሁ፣ ለወንድሞቻችሁ ቅን ፍቅር ይኑራችሁ፤ እርስ በርሳችሁም አጥብቃችሁ ከልብ#1፥22 አንዳንድ የጥንት ቅጆች ከንጹሕ ልብ ይላሉ። ተዋደዱ። 23ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር ሳይሆን፣ ሕያው በሆነና ጸንቶ በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል አማካይነት ከማይጠፋ ዘር ነው። 24ምክንያቱም መጽሐፍ እንደሚል፣
“ሥጋ ለባሽ ሁሉ እንደ ሣር ነው፤
ክብሩም ሁሉ እንደ ሜዳ አበባ ነው።
ሣሩ ይጠወልጋል፤ አበባውም ይረግፋል፤
25የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”#1፥25 ኢሳ 40፥6-8 (ሰባ ሊቃናትን ይመልከቱ)
የተሰበከላችሁም የምሥራች ቃል ይህ ነው።
Currently Selected:
1 ጴጥሮስ 1: NASV
Highlight
Share
Copy
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fen.png&w=128&q=75)
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.