1 ጢሞቴዎስ 4
4
1በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች እምነትን ክደው አታላይ መናፍስትንና የአጋንንትን ትምህርት እንደሚከተሉ መንፈስ በግልጽ ይናገራል። 2እንዲህ ያለው ትምህርት የሚመጣው ኅሊናቸው በጋለ ብረት የተጠበሰ ያህል ከደነዘዘባቸው ግብዝ ውሸተኞች ነው። 3እነርሱ፣ ሰዎች እንዳያገቡ ይከለክላሉ፤ የሚያምኑና እውነትን የሚያውቁ ሰዎች እግዚአብሔር የፈጠረውን፣ በምስጋናም የሚቀበሉትን እንዳይበሉ ያዝዛሉ። 4እግዚአብሔር የፈጠረው ማንኛውም ነገር መልካም ነውና፤ በምስጋና ከተቀበሉትም የሚጣል ምንም ነገር የለም፣ 5በእግዚአብሔር ቃልና በጸሎት የተቀደሰ ነውና።
6ይህን ትእዛዝ ለወንድሞች#4፥6 ወንድሞች የሚለው የግሪኩ ቃል ወንዶችን ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ቤተ ሰብ አካል በመሆናቸው ያመኑትን ወንዶችንና ሴቶችንም ያመለክታል። ብታሳስብ፣ በእምነት ቃልና በተቀበልኸው መልካም ትምህርት ታንጸህ የክርስቶስ ኢየሱስ በጎ አገልጋይ ትሆናለህ። 7እግዚአብሔርን ከማያከብር ርባና ቢስ አፈ ታሪክና ከአሮጊቶች ተረታ ተረት ራቅ፤ ይልቁንም ለእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ራስህን አሠልጥን። 8የአካል ብቃት ልምምድ ለጥቂት ነገር ይጠቅማልና፤ ለእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ራስን ማሠልጠን ግን ለአሁኑም ሆነ ለሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው ለሁለቱም ይጠቅማል። 9ይህ ቃል የታመነና ሙሉ ለሙሉ ሊቀበሉት የሚገባ ነው። 10ለዚህ ብለን እንጥራለን፤ እንደክማለንም፤ ይኸውም ለሰዎች ሁሉ፣ በተለይም ለሚያምኑት አዳኝ በሆነው በሕያው እግዚአብሔር ተስፋ ስለምናደርግ ነው።
11እነዚህን ነገሮች እዘዝ፤ አስተምርም። 12ወጣትነትህን ማንም አይናቅ፤ ነገር ግን ለሚያምኑት በንግግርና በኑሮ፣ በፍቅር፣ በእምነትና በንጽሕና አርኣያ ሁንላቸው። 13እኔ እስክመጣ ድረስ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለሕዝብ ለማንበብ፣ ለመምከርና ለማስተማር ትጋ። 14ሽማግሌዎች እጃቸውን በአንተ ላይ ሲጭኑ በትንቢት የተሰጠህን የጸጋ ስጦታ ቸል አትበል።
15ሰው ሁሉ ማደግህን ያይ ዘንድ በእነዚህ ነገሮች ላይ አትኵር፤ በትጋትም ፈጽማቸው። 16ለሕይወትህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፤ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፣ ራስህንና የሚሰሙህንም ታድናለህና።
Currently Selected:
1 ጢሞቴዎስ 4: NASV
Highlight
Share
Copy

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.