YouVersion Logo
Search Icon

2 ሳሙኤል 5

5
ዳዊት በእስራኤል ላይ ነገሠ
5፥1-3 ተጓ ምብ – 1ዜና 11፥1-3
1የእስራኤል ነገዶች በሙሉ ወደ ኬብሮን ወደ ዳዊት መጥተው እንዲህ አሉ፤ “እነሆ፤ እኛ የዐጥንትህ ፍላጭ፣ የሥጋህ ቍራጭ ነን፤ 2በቀደመው ዘመን ሳኦል በእኛ ላይ ንጉሥ በነበረ ጊዜ፣ እስራኤልን በጦርነት የምትመራ አንተ ነበርህ፤ እግዚአብሔርም፣ ‘ሕዝቤን እስራኤልን ትጠብቃለህ፤ መሪያቸውም ትሆናለህ’ ብሎህ ነበር።”
3ስለዚህ የእስራኤል ሽማግሌዎች በሙሉ ንጉሥ ዳዊት ወዳለበት ወደ ኬብሮን መጡ፤ ዳዊትም በኬብሮን በእግዚአብሔር ፊት ከእነርሱ ጋራ ቃል ኪዳን አደረገ፤ እነርሱም ዳዊትን ቀብተው በእስራኤል ላይ አነገሡት።
4ዳዊት በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበረ፤ አርባ ዓመትም ገዛ። 5በኬብሮን ተቀምጦ በይሁዳ ላይ ሰባት ዓመት ከስድስት ወር፣ ኢየሩሳሌም ሆኖም በመላው እስራኤልና በይሁዳ ላይ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነገሠ።
ዳዊት ኢየሩሳሌምን ድል አደረገ
5፥6-10 ተጓ ምብ – 1ዜና 11፥4-9
5፥11-16 ተጓ ምብ – 1ዜና 3፥5-914፥1-7
6ንጉሡና ሰዎቹ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያንን ለመውጋት ወደዚያ ሄዱ። ኢያቡሳውያንም፣ “ዳዊት እዚህ ሊገባ አይችልም” ብለው ስላሰቡ ዳዊትን፣ “ዕውሮችና ዐንካሶች እንኳ ይከለክሉሃልና ወደዚህች አትገባም” አሉት። 7ይሁን እንጂ ዳዊት የጽዮንን ዐምባ ያዘ፤ ይህችም የዳዊት ከተማ የተባለችው ናት።
8በዚያም ዕለት ዳዊት፣ “ኢያቡሳውያንን ድል ማድረግ የሚፈልግ፣ የዳዊት ጠላቶች#5፥8 ወይም ማንጠልጠያ ኵላቦች ወደሚሆኑ፣ ‘ዐንካሶችና ዕውሮች’ ለመድረስ በውሃ መተላለፊያው#5፥8 ወይም በዳዊት የተጠላ ሽቅብ መውጣት አለበት” አለ። እንግዲህ፣ “ ‘ዐንካሶችና ዕውሮች’ ወደ ቤተ መንግሥት አይገቡም” ያሉት ለዚህ ነው።
9ከዚያም ዳዊት መኖሪያውን በዐምባዪቱ ላይ አደረገ፤ የዳዊት ከተማም ብሎ ጠራት። ዳዊትም ከሚሎ አንሥቶ ወደ ውስጥ ዙሪያዋን ገነባት። 10የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ ስለ ነበር፣ ዳዊት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ ሄደ።
11በዚህ ጊዜ የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ወደ ዳዊት መልክተኞችን ላከ፤ እንዲሁም የዝግባ ዕንጨት፣ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችና ድንጋይ ጠራቢዎችን ዐብሮ ሰደደ፤ እነርሱም ለዳዊት ቤተ መንግሥት ሠሩለት። 12ዳዊትም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥነቱን እንዳጸናለት፣ ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤልም ሲል መንግሥቱን ከፍ ከፍ እንዳደረገለት ተገነዘበ።
13ዳዊት ከኬብሮን ከሄደ በኋላ፣ በኢየሩሳሌም ተጨማሪ ሚስቶች አገባ፤ ቁባቶችንም አስቀመጠ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ተወለዱለት። 14በኢየሩሳሌም የተወለዱለትም ልጆች ሳሙስ፣ ሶባብ፣ ናታን፣ ሰሎሞን፣ 15ኢያቤሐር፣ ኤሊሱዔ፣ ናፌቅ፣ ያፍያ፣ 16ኤሊሳማ፣ ኤሊዳሄ፣ ኤሊፋላት ይባላሉ።
ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን ድል አደረገ
5፥17-25 ተጓ ምብ – 1ዜና 14፥8-17
17ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ንጉሥ ሆኖ መቀባቱን ፍልስጥኤማውያን በሰሙ ጊዜ፣ እርሱን ፍለጋ በሙሉ ኀይላቸው ወጡ፤ ዳዊትም ይህን ሰምቶ ወደ ምሽጉ ወረደ። 18በዚህ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን መጥተው በራፋይም ሸለቆ ተበታትነው ሰፈሩ። 19ስለዚህም ዳዊት፣ “በፍልስጥኤማውያን ላይ ወጥቼ ልምታቸውን? በእጄስ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ።
እግዚአብሔርም፣ “አዎን ሂድ፤ በርግጥ ፍልስጥኤማውያንን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ” አለው።
20ስለዚህም ዳዊት ወደ በኣልፐራሲም#5፥20 በኣልፐራሲም ማለት የሚሰባበር ጌታ ማለት ነው። ሄዶ ፍልስጥኤማውያንን ድል አደረጋቸው። እርሱም “የጐርፍ ውሃ ጥሶ በመውጣት እንደሚያፈራርስ፣ እግዚአብሔርም ጠላቶቼን በፊቴ አፈራረሳቸው” አለ። ከዚህ የተነሣም የዚያ ቦታ ስም “በኣልፐራሲም” ተባለ። 21ፍልስጥኤማውያንም ጣዖቶቻቸውን ትተው ሸሽተው ስለ ነበር፣ ዳዊትና ሰዎቹ ወስደው አቃጠሏቸው።
22ፍልስጥኤማውያን እንደ ገና መጥተው በራፋይም ሸለቆ ተበታትነው ሰፈሩ። 23ስለዚህም ዳዊት እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “በስተ ኋላቸው በኩል በመክበብ በሾላው ዛፍ ፊት ለፊት ግጠማቸው እንጂ በቀጥታ ወዳሉበት አትውጣ፤ 24በሾላ ዛፎች ጫፍ ላይ የሰልፍ ጕዞ ድምፅ ስትሰማም፣ እግዚአብሔር የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት ለመምታት ቀድሞህ ወጥቷል ማለት ነውና በዚያ ጊዜ በፍጥነት ወደ ፊት ሂድ።” 25ስለዚህም ዳዊት እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ፍልስጥኤማውያንንም ከገባዖን#5፥25 የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ከዚህ ጋራ ይስማማል (1ዜና 14፥16 ይመ)፤ ዕብራይስጡ ግን፣ ጊባ ይላል። እስከ ጌዝር ድረስ እያሳደደ መታቸው።

Currently Selected:

2 ሳሙኤል 5: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in