2 ሳሙኤል 7
7
እግዚአብሔር ለዳዊት የሰጠው ተስፋ
7፥1-17 ተጓ ምብ – 1ዜና 17፥1-15
1ንጉሡ በቤተ መንግሥቱ ተደላድሎ ከተቀመጠና እግዚአብሔርም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ ካሳረፈው በኋላ፣ 2ንጉሡ ነቢዩ ናታንን፣ “እነሆ፤ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤተ መንግሥት ውስጥ እኖራለሁ፤ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ይኖራል” አለው።
3ናታንም፣ ንጉሡን “እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ስለ ሆነ፣ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ” ሲል መለሰለት።
4በዚያች ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን እንዲህ ሲል መጣ፤
5“ሂድና ባሪያዬን ዳዊትን፣ ‘እንዲህ ብለህ ንገረው፤ እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ የምኖርበትን ቤት የምትሠራልኝ አንተ ነህን? በለው። 6እስራኤላውያንን ከግብጽ ምድር ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ድንኳንን ማደሪያዬ አድርጌ ከቦታ ወደ ቦታ ተጓዝሁ እንጂ በቤት ውስጥ አልተቀመጥሁም። 7በእስራኤል ሕዝብ መካከል ባለፍሁባቸው ቦታዎች ሁሉ፣ ሕዝቤን እስራኤልን እንዲጠብቁ ካዘዝኋቸው ነገዶች#7፥7 በዚህና በቍጥር 10 ላይ በትውፊት፣ መሳፍንት ይባላል። “ለምን ከዝግባ ዕንጨት ቤት አልሠራችሁልኝም” ያልሁት አለን?’
8“አሁንም ባሪያዬ ዳዊትን እንዲህ በለው፤ ‘የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ገዥ እንድትሆን ከሜዳ አነሣሁህ፤ ከበግ ጥበቃም ወሰድሁህ፤ 9በሄድህበት ሁሉ እኔ ከአንተ ጋራ ነበርሁ፤ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁልህ፤ አሁንም ስማቸው በምድር ላይ ከገነነው እጅግ ታላላቅ ሰዎች እንደ አንዱ ስምህን ገናና አደርገዋለሁ፤ 10የራሳቸውም መኖሪያ ስፍራ እንዲኖራቸው፣ ከእንግዲህ በኋላም እንዳይናወጡ ለሕዝቤ ለእስራኤል መኖሪያ ስፍራ እሰጣቸዋለሁ። ከዚህ ቀደም እንዳደረጉት ክፉዎች ከእንግዲህ አይጨቍኗቸውም፤ 11ለሕዝቤ ለእስራኤልም መሪዎች#7፥11 በትውፊት፣ መሳፍንት ይባላል ከሾምሁለት ጊዜ አንሥቶ ያደረጉትን ዛሬ አያደርጉበትም፤ እንዲሁም ከጠላቶችህ ሁሉ እጠብቅሃለሁ።
“ ‘እግዚአብሔር ራሱ ቤት እንደሚሠራልህ ይነግርሃል፤ 12ዘመንህን ጨርሰህ ከአባቶችህ ጋራ በምታንቀላፋበት ጊዜ፣ በእግርህ እንዲተካ ከአብራክህ የተከፈለ ዘር አስነሣልሃለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ። 13ለስሜ ቤት የሚሠራልኝም እርሱ ነው፤ እኔም የመንግሥቱን ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ። 14አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጄ ይሆናል። በደል ቢፈጽም ግን ሰዎች በሚቀጡበት በትር እቀጣዋለሁ፤ የሰው ልጆችም በዐለንጋ እንደሚገረፉ እገርፈዋለሁ። 15ምሕረቴን ከአንተ በፊት ካስወገድሁት ከሳኦል እንዳራቅሁ ሁሉ ከርሱ አላርቅም። 16ቤትህና መንግሥትህ በፊቴ#7፥16 አንዳንድ የዕብራይስጥ ቅጆችና የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ከዚህ ጋራ ይስማማሉ፤ አብዛኞቹ የዕብራይስጥ ቅጆች ግን፣ በፊትህ ይላሉ። ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤ ዙፋንህም እንደዚሁ ለዘላለም የጸና ይሆናል።’ ”
17ናታንም የዚህን ራእይ ቃል በሙሉ፣ ለዳዊት ነገረው።
የዳዊት ጸሎት
7፥18-29 ተጓ ምብ – 1ዜና 17፥16-27
18ከዚያም ንጉሥ ዳዊት ገባ፤ በእግዚአብሔር ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ፤
“ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድን ነው? 19ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህ በፊትህ ጥቂት ሆኖ ሳለ አንተ ግን ስለ ወደ ፊቱ የባሪያህ ቤት ተናገርህ፤ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ከሰው#7፥19 ወይም ለሰው ልጅ ጋራ የምታደርገው ግንኙነት ለካ እንዲህ ነው?
20“ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ሊልህ ይችላል? ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ባሪያህን አንተ ታውቀዋለህ፤ 21ስለ ቃልህና እንደ ልብህ ሐሳብ ይህን ታላቅ ነገር አድርገሃል፤ ባሪያህም እንዲያውቀው ገልጸህለታል።
22“ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዴት ታላቅ ነህ! እንደ አንተ ያለ ማንም የለም፤ በጆሯችን እንደ ሰማነው ሁሉ፣ ከአንተ በቀር አምላክ የለም።
23“ለራሱ ሕዝብ ይሆን ዘንድ ሊታደገው፣ እግዚአብሔር በፊቱ እንደሄደለት ሕዝብ፣ ለራሱም ስም ያደርግ ዘንድ አሕዛብንና አማልክታቸውን ከፊቱ አሳድዶ ታላላቅና አስፈሪ ታምራት እንዳደረገለትና ከግብጽም እንደ ተቤዠው እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ማን አለ? 24ሕዝብህን እስራኤልን ለዘላለም የራስህ ሕዝብ አድርገህ አጽንተኸዋል፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተም አምላክ ሆነኸዋል።
25“አሁንም እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ ለባሪያህና ለቤቱ የሰጠኸውን ተስፋ ለዘላለም የጸና ይሁን፤ እንደተናገርኸውም ፈጽም፤ 26ስለዚህ ስምህ ለዘላለም ታላቅ ይሆናል፤ ሰዎችም፣ ‘የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ነው!’ ይላሉ። የባሪያህ የዳዊትም ቤት በፊትህ የጸና ይሆናል።
27“አቤቱ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ‘እኔ ለአንተ ቤት እሠራልሃለሁ’ ብለህ ይህን ለባሪያህ ገልጸህለታል። ስለዚህ ባሪያህ ይህችን ጸሎት ወደ አንተ ለማቅረብ በልቡ ደፈረ። 28አሁንም ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላክ ነህ፤ ቃልህም የታመነ ነው፤ ይህንም መልካም ነገር ለማድረግ ለባሪያህ ተስፋ ሰጥተኸዋል፤ 29በፊትህ ለዘላለም ጸንቶ እንዲኖር፣ አሁንም የባሪያህን ቤት እባክህ ባርክ። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህን አንተው ራስህ ተናግረሃል፤ በበረከትህም የባሪያህ ቤት ለዘላለም ይባረካል።”
Currently Selected:
2 ሳሙኤል 7: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.