ቈላስይስ 3
3
የቅድስና ሕይወት መመሪያ
1እንግዲህ ከክርስቶስ ጋራ ከተነሣችሁ፣ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ በተቀመጠበት በላይ ያሉ ነገሮችን ፈልጉ፤ 2ሐሳባችሁም በላይ ባለው ላይ እንጂ በምድራዊ ነገር ላይ አይሁን። 3ሞታችኋልና፤ ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋራ በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰውሯልና፤ 4ሕይወታችሁ#3፥4 አንዳንድ የጥንት ቅጆች የኛ ሕይወት የሆነው ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ እናንተም በዚያ ጊዜ ከርሱ ጋራ በክብር ትገለጣላችሁ።
5ስለዚህ ምድራዊ ምኞቶቻችሁን ግደሉ፤ እነዚህም፦ ዝሙት፣ ርኩሰት፣ ፍትወት፣ ክፉ ምኞትና አምልኮተ ጣዖት የሆነው መጐምጀት ናቸው። 6በእነዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ቍጣ በማይታዘዙት#3፥6 በማይታዘዙት ላይ የሚለው ሐረግ በአንዳንድ የጥንት ቅጆች ላይ ብቻ የሚገኝ ነው። ላይ ይመጣል፤ 7እናንተም ቀድሞ በኖራችሁበት ሕይወት በእነዚህ ትመላለሱ ነበር፤ 8አሁን ግን ቍጣን፣ ንዴትን፣ ክፋትን፣ ስድብንና አሳፋሪ ንግግርን የመሳሰሉትንም ሁሉ አስወግዱ፤ 9አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋራ አውልቃችሁ ስለ ጣላችሁ እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ። 10የፈጣሪውን መልክ እንዲመስል በዕውቀት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችኋል፤ 11በዚያ ግሪክ ወይም ይሁዲ፣ የተገረዘ ወይም ያልተገረዘ፣ አረማዊ ወይም እስኩቴስ፣ ባሪያ ወይም ጌታ ብሎ ልዩነት የለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉም ነው፤ በሁሉም ነው።
12እንግዲህ የተቀደሳችሁና የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ምርጦች እንደ መሆናችሁ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ ጨዋነትንና ትዕግሥትን ልበሱ፤ 13እርስ በርሳችሁም ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሠኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ሌላውን ይቅር በሉ። 14በእነዚህ ሁሉ ላይ ሁሉን በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረውን ፍቅርን ልበሱት።
15እንደ አንድ አካል ሆናችሁ የተጠራችሁበት የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይንገሥ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። 16የክርስቶስ ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ እርስ በርሳችሁ በጥበብ ሁሉ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በማሕሌት፣ በመንፈሳዊም ቅኔ በማመስገን በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ። 17በርሱ በኩል ለእግዚአብሔር አብ ምስጋና እያቀረባችሁ፣ በቃልም ሆነ በተግባር የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት።
የክርስቲያናዊ ቤተ ሰብ መመሪያ
18ሚስቶች ሆይ፤ በጌታ ዘንድ ተገቢ በመሆኑ ለባሎቻችሁ ተገዙ።
19ባሎች ሆይ፤ ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ መራራም አትሁኑባቸው።
20ልጆች ሆይ፤ ይህ ጌታን ደስ የሚያሰኝ በመሆኑ በሁሉም ነገር ለወላጆቻችሁ ታዘዙ።
21አባቶች ሆይ#3፥21 ወላጆች ሆይ፤ ተስፋ እንዳይቈርጡ ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው።
22ባሮች ሆይ፤ ለታይታ ሰውን እንደሚያስደስቱት ሳይሆን፣ በቅን ልብ ጌታን በመፍራት ለምድራዊ ጌቶቻችሁ በሁሉ ነገር ታዘዙ። 23የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉት ቈጥራችሁ በሙሉ ልባችሁ አድርጉት፤ 24ከጌታ ዘንድ እንደ ብድራት የምትቀበሉት ርስት እንዳለ ታውቃላችሁና፤ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስን ነው። 25በደለኛውም የእጁን ያገኛል፤ አድልዎም የለም።
Currently Selected:
ቈላስይስ 3: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.