YouVersion Logo
Search Icon

ዕብራውያን 12

12
1እንግዲህ እነዚህን የመሳሰሉ ብዙ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፣ ሸክም የሚሆንብንን ሁሉ፣ በቀላሉም ተብትቦ የሚይዘንን ኀጢአት አስወግደን በፊታችን ያለውን ሩጫ በጽናት እንሩጥ። 2የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን እንመልከት፤ እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ፣ የመስቀሉንም ውርደት ንቆ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል። 3እንግዲህ ዝላችሁ ተስፋ እንዳትቈርጡ፣ ከኀጢአተኞች የደረሰበትን እንዲህ ያለውን ተቃውሞ የታገሠውን እርሱን አስቡ።
እግዚአብሔር ልጆቹን ይቀጣል
4ከኀጢአት ጋራ ስትታገሉ ገና ደማችሁን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም። 5ልጆች እንደ መሆናችሁ እንዲህ በማለት የተናገራችሁን ማበረታቻ ቃልም ረስታችኋል፦
“ልጄ ሆይ፤ የጌታን ተግሣጽ አታቃልል፤
በሚቀጣህም ጊዜ ተስፋ አትቍረጥ፤
6ምክንያቱም ጌታ የሚወድደውን ይገሥጻል፤
እንደ ልጅ የሚቀበለውንም ይቀጣል።”#12፥6 ምሳ 3፥11፤ 12 (ሰባ ሊቃናት ይመልከቱ)
7እግዚአብሔር እንደ ልጆቹ ይዟችኋልና የተግሣጽን ምክር ታገሡ፤ ለመሆኑ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው? 8ልጆች ሁሉ በሚቀጡበት ቅጣት ተካፋይ ካልሆናችሁ፣ ዲቃሎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም። 9ከዚህም በላይ፣ እኛ ሁላችን የሚቀጡን ምድራዊ አባቶች ነበሩን፤ እናከብራቸውም ነበር። ታዲያ ለመናፍስት አባት እንዴት አብልጠን በመገዛት በሕይወት አንኖርም! 10አባቶቻችን መልካም መስሎ እንደ ታያቸው ለጥቂት ጊዜ ይቀጡን ነበር፤ እግዚአብሔር ግን የቅድስናው ተካፋዮች እንድንሆን ለእኛ ጥቅም ሲል ይቀጣናል። 11ቅጣት ሁሉ በወቅቱ የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፤ በኋላ ግን ለለመዱት ሰዎች የጽድቅና የሰላም ፍሬ ያስገኝላቸዋል።
12ስለዚህ የዛለውን ክንዳችሁንና የደከመውን ጕልበታችሁን አበርቱ። 13ዐንካሳው እንዲፈወስ እንጂ የባሰውኑ እንዳያነክስ “ለእግራችሁ ቀና መንገድ አብጁ።”#12፥13 ምሳ 4፥26
እግዚአብሔርን ስላለመታዘዝ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
14ከሰው ሁሉ ጋራ በሰላም ለመኖር የሚቻላችሁን ሁሉ አድርጉ፤ ለመቀደስም ፈልጉ፤ ያለ ቅድስና ማንም ጌታን ማየት አይችልም። 15ከእናንተ ማንም የእግዚአብሔር ጸጋ እንዳይጐድልበት፣ ደግሞም መራራ ሥር በቅሎ ችግር እንዳያስከትልና ብዙዎችን እንዳይበክል ተጠንቀቁ። 16ለአንድ ጊዜ መብል ሲል ብኵርናውን እንደ ሸጠው እንደ ዔሳው፣ ማንም ሴሰኛ ወይም እግዚአብሔርን የማያከብር ሆኖ እንዳይገኝ ተጠንቀቁ። 17በኋላም ይህንኑ በረከት ሊወርስ በፈለገ ጊዜ እንደ ተከለከለ ታውቃላችሁ፤ በረከቱን በእንባ ተግቶ ቢፈልግም ለንስሓ ስፍራ ሊያገኝ አልቻለም።
የፍርሀት ተራራና የደስታ ተራራ
18ሊዳሰስ ወደሚችለውና በእሳት ወደሚቃጠለው ተራራ፣ ወደ ጨለማው፣ ወደ ጭጋጉና ወደ ዐውሎ ነፋሱ አልደረሳችሁም፤ 19ወደ መለከት ድምፅ ወይም ቃልን ወደሚያሰማ ድምፅ አልመጣችሁም፤ የሰሙትም ሌላ ቃል ተጨምሮ እንዳይናገራቸው ለመኑ። 20ምክንያቱም “እንስሳ እንኳ ተራራውን ቢነካ፣ በድንጋይ ተወግሮ ይሙት”#12፥20 ዘፀ 19፥12፤ 13 የሚለውን ትእዛዝ መሸከም አልቻሉም። 21በዚያ ይታይ የነበረውም ሁኔታ እጅግ አስፈሪ ነበርና፣ ሙሴ “በፍርሀት ተንቀጠቀጥሁ”#12፥21 ዘዳ 9፥19። አለ።
22እናንተ ግን ወደ ጽዮን ተራራ፣ ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም፣ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ መጥታችኋል፤ በደስታ ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፣ 23ስማቸው በሰማይ ወደ ተጻፈው ወደ በኵራት ማኅበር ቀርባችኋል፤ የሁሉ ዳኛ ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር፣ ፍጹምነትን ወዳገኙት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፣ 24የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ወደ ሆነው ወደ ኢየሱስ፣ እንዲሁም ከአቤል ደም የተሻለ ቃል ወደሚናገረው ወደ ተረጨው ደም ደርሳችኋል።
25የሚናገረውን እርሱን እንቢ እንዳትሉት ተጠንቀቁ። እነዚያ ከምድር ሆኖ ሲያስጠነቅቃቸው የነበረውን እንቢ ባሉ ጊዜ ካላመለጡ፣ እኛ ከሰማይ የመጣው ሲያስጠነቅቀን ከርሱ ብንርቅ እንዴት ልናመልጥ እንችላለን? 26በዚያ ጊዜ ድምፁ ያናወጠው ምድርን ነበር፤ አሁን ግን፣ “አንድ ጊዜ እንደ ገና ምድርን ብቻ ሳይሆን፣ ሰማያትንም አናውጣለሁ”#12፥26 ሐጌ 2፥6 ብሎ ቃል ገብቷል። 27አንድ ጊዜ “ደግሜ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው የማይናወጡት ጸንተው ይኖሩ ዘንድ፣ የሚናወጡት ይኸውም፣ የተፈጠሩት የሚወገዱ መሆናቸውን ነው።
28ስለዚህ ከቶ የማይናወጥ መንግሥት ስለምንቀበል እግዚአብሔርን እናመስግን፤ ደግሞም ደስ በሚያሠኘው መንገድ በአክብሮትና በፍርሀት እናምልከው፤ 29“አምላካችን የሚባላ እሳት ነውና።”#12፥29 ዘዳ 4፥24

Currently Selected:

ዕብራውያን 12: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in