YouVersion Logo
Search Icon

ኢሳይያስ 38

38
የሕዝቅያስ መታመም
1በዚያ ጊዜ ሕዝቅያስ በጠና ታምሞ፤ ሊሞት ተቃርቦ ነበር። የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስም ወደ እርሱ መጥቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ከሕመምህ አትድንም፤ ትሞታለህና ቤትህን አስተካክል’ ” አለው።
2ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳ አዙሮ፣ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ 3እግዚአብሔር ሆይ፤ በፊትህ በታማኝነትና በፍጹም ልብ እንደ ሄድሁ፤ ደስ የሚያሰኝህንም እንዳደረግሁ ዐስብ።” ሕዝቅያስም አምርሮ አለቀሰ።
4እግዚአብሔርም ቃል ወደ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል መጣ፤ 5“ሂድና ለሕዝቅያስ እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ እንባህንም አይቻለሁ፤ በዕድሜህም ላይ ዐሥራ ዐምስት ዓመት እጨምርልሃለሁ። 6አንተንና ይህችን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፤ ይህችን ከተማ እከላከልላታለሁ።
7“ ‘እግዚአብሔር የገባልህን ቃል እንደሚፈጽምልህ፣ የእግዚአብሔር ምልክት ይህ ነው፤ 8በአካዝ የሰዓት መቍጠሪያ ደረጃ ላይ፣ የወረደውን የፀሓይ ጥላ በዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደርጋለሁ።’ ” ስለዚህ ወርዶ የነበረው የፀሓይ ጥላ ያንኑ ያህል ወደ ኋላ ተመለሰ።
9የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ከሕመሙ ከተፈወሰ በኋላ የጻፈው ጽሕፈት፤
10እኔ፣ “በዕድሜዬ እኩሌታ፣
በሲኦል ደጆች ማለፍ አለብኝን?
የቀረውንስ ዘመኔን ልነጠቅ ይገባልን?” አልሁ።
11እንዲህም አልሁ፤ “ዳግም እግዚአብሔርን፣
እግዚአብሔርን በሕያዋን ምድር አላይም፤
ከእንግዲህም የሰውን ዘር አላይም፤
በዚህ ዓለም ከሚኖሩትም ጋራ አልሆንም።
12ቤቴ እንደ እረኛ ድንኳን ተነቀለ፤
ከእኔም ተወሰደ፤
ሕይወቴን እንደ ሸማኔ ጠቀለልሁ፤
ከመጠቅለያ ቈርጦኛል፤
ከጧት እስከ ማታ ልትጨርሰኝ ፈጠንህ።
13እስከ ማለዳ በትዕግሥት ጠበቅሁ፤
እርሱ ግን እንደ አንበሳ ዐጥንቶቼን ሁሉ ሰባበረ፤
ከጧት እስከ ማታም ልትጨርሰኝ ፈጠንህ።
14እንደ ጨረባ፣ እንደ ሽመላም ተንጫጫሁ፤
እንደ ርግብ አልጐመጐምሁ፤
ዐይኖቼ ወደ ሰማይ በመመልከት ደከሙ፤
ጌታ ሆይ፤ ተጨንቄአለሁና ታደገኝ!”
15እንግዲህ ምን እላለሁ?
እርሱ ተናግሮኛል፤ ራሱ ደግሞ ይህን አድርጓል፤
ስለ ነፍሴ ጭንቀት፣
ዕድሜዬን ሁሉ በትሕትና እሄዳለሁ።
16ጌታ ሆይ፤ ሰዎች በእነዚህ ነገሮች ይኖራሉ፤
መንፈሴም እንዲሁ በእነዚህ ሕይወትን ያገኛል፤
ፈወስኸኝ፤
በሕይወትም አኖርኸኝ።
17እነሆ፤ በሥቃይ የተጨነቅሁት፣
ለጥቅሜ ሆነ፤
ከጥፋት ጕድጓድ፣
በፍቅርህ ጠበቅኸኝ፤
ኀጢአቴንም ሁሉ፣
ወደ ኋላህ ጣልህ።
18ሲኦል አያመሰግንህም፤
ሞት አያወድስህም፤
ወደ ጕድጓድ የሚወርዱ፣
የአንተን ታማኝነት ተስፋ አያደርጉም።
19እኔ ዛሬ እንደማደርገው፣
ሕያዋን እነርሱ ያመሰግኑሃል።
ስለ አንተ ታማኝነትም፣
አባቶች ለልጆቻቸው ይነግራሉ።
20 እግዚአብሔር ያድነኛል፤
ስለዚህ በዕድሜ ዘመናችን ሁሉ፣
እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣
አውታር ባለው መሣሪያ እንዘምራለን።
21ኢሳይያስም፣ “የበለስ ጥፍጥፍ ወስዳችሁ በዕባጩ ላይ አድርጉለት፤ እርሱም ይፈወሳል” ብሎ ነበር።
22ሕዝቅያስም፣ “ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እወጣ ዘንድ ምልክቱ ምንድን ነው?” ብሎ ነበር።

Currently Selected:

ኢሳይያስ 38: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Video for ኢሳይያስ 38