YouVersion Logo
Search Icon

ኤርምያስ 8

8
1“ ‘በዚያ ጊዜ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ የይሁዳ ነገሥታትና መኳንንት ዐፅም፣ የካህናትና የነቢያት ዐፅም፣ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ዐፅም ከየመቃብራቸው ይወጣል። 2በወደዷቸውና በአገለገሏቸው እንዲሁም በተከተሏቸው፣ ባማከሯቸውና ባመለኳቸው በፀሓይ፣ በጨረቃና በሰማያት ከዋክብት ሁሉ ፊት ይሰጣል፤ አይሰበሰብም ወይም አይቀበርም፤ ነገር ግን እንደ ተጣለ ጕድፍ በምድር ላይ ይበተናል። 3ከዚህ ክፉ ሕዝብ የተረፉት ሁሉ፣ ባሳደድኋቸው ስፍራ ሁሉ ከሕይወት ይልቅ ሞትን ይመርጣሉ፤ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።’
ኀጢአትና ያስከተለው ቅጣት
4“እንዲህ በላቸው፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“ ‘ሰዎች ቢውድቁ፣ እንደ ገና ከወደቁበት አይነሡምን?
ሰው ተሳስቶ ወደ ኋላ ቢሄድ፣ ከስሕተቱ አይመለስምን?
5ታዲያ፣ ይህ ሕዝብ ለምን ፊቱን አዙሮ ወደ ኋላ ይሄዳል?
ለምንስ ኢየሩሳሌም ዘወትር ወደ ኋላ ትመለሳለች?
ተንኰልን የሙጥኝ ብለው ይዘዋል፤
ሊመለሱም ፈቃደኛ አይደሉም።
6እኔ በጥንቃቄ አደመጥኋቸው፤
ትክክለኛ የሆነውን ግን አይናገሩም።
ማንም ስለ ክፋቱ ንስሓ የገባ የለም፤
“ምን አድርጌአለሁ?” ይላል።
ለጦርነት እንደ ተዘጋጀ ፈረስ፣
እያንዳንዱ በራሱ መንገድ ይሄዳል።
7ሽመላ እንኳ በሰማይ፣
የተወሰነ ጊዜዋን ታውቃለች፤
ዋኖስ፣ ጨረባና ዋርዳም፣
የሚሰደዱበትን ጊዜ ያውቃሉ፤
ሕዝቤ ግን፣
እግዚአብሔርን ሥርዐት አላወቀም።
8“ ‘የጸሓፊዎቻችሁ ሐሰተኛ ብርዕ ሐሰት
እያስተናገደ እንዴት፣ “ዐዋቂዎች ነን፣
እግዚአብሔር ሕግ አለን” ትላላችሁ?
9ጥበበኞች ያፍራሉ፤
ይዋረዳሉ፤ በወጥመድም ይያዛሉ።
እግዚአብሔርን ቃል ተቃውመው፣
ምን ዐይነት ጥበብ ይኖራቸዋል?
10ስለዚህ ሚስቶቻቸውንም ለሌሎች ወንዶች እሰጣለሁ፤
ዕርሻዎቻቸውንም ለባዕዳን እሰጣለሁ፤
ከታናሹ እስከ ታላቁ ድረስ፣
ሁሉም ተገቢ ላልሆነ ጥቅም ይስገበገባሉ፤
ነቢያትና ካህናትም እንዲሁ፤
ሁሉም ያጭበረብራሉ።
11የሕዝቤን ቍስል ብርቱ እንዳይደለ በመቍጠር፣
የተሟላ ፈውስ ሳይኖር እንዲሁ ያክማሉ፤
ሰላም ሳይኖር፣
“ሰላም፣ ሰላም” ይላሉ።
12ስለ ጸያፉ ተግባራቸው ዐፍረዋል እንዴ?
የለም! በጭራሽ አላፈሩም፤
ዕፍረት ምን እንደ ሆነ እንኳ አያውቁም።
ስለዚህ ከወደቁት ጋራ ይወድቃሉ፤
በሚቀጡ ጊዜ ይዋረዳሉ፣
ይላል እግዚአብሔር
13“ ‘ያመረቱትን ሁሉ እወስድባቸዋለሁ፤
ይላል እግዚአብሔር
በወይን ተክል ላይ የወይን ፍሬ አይኖርም፤
በበለስ ዛፍ ላይ የበለስ ፍሬ አይገኝም፤
ቅጠሎቻቸውም ይረግፋሉ።
የሰጠኋቸው በሙሉ፣
ከእነርሱ ይወሰድባቸዋል።#8፥13 በዕብራይስጡ የዚህ ስንኝ ወይም ዐረፍተ ነገር ትርጕም በግልጽ አይታወቅም።’ ”
14ለምን እዚህ እንቀመጣለን?
በአንድነት ተሰብሰቡ!
ወደ ተመሸጉት ከተሞች እንሽሽ፤
በዚያም እንጥፋ!
በርሱ ላይ ኀጢአትን ስላደረግን፣
እግዚአብሔር አምላካችን እንድንጠፋ አድርጎናል፤
የተመረዘ ውሃ እንድንጠጣ ሰጥቶናል።
15ሰላምን ተስፋ አደረግን፤
መልካም ነገር ግን አልመጣም፤
የፈውስ ጊዜን ተመኘን፤
ነገር ግን ሽብር ብቻ ሆነብን።
16የጠላት ፈረሶች ፉርፉርታ፣
ከዳን ይሰማል፤
በድንጉላ ፈረሶቻቸው ማሽካካት፣
መላዋ ምድር ተንቀጠቀጠች።
ምድሪቱንና በውስጧ ያለውን ሁሉ፣
ከተማዪቱንና በውስጧ የሚኖሩትን ሁሉ፣
ሊውጡ መጡ።
17“እነሆ፤ በመካከላችሁ መርዘኛ እባቦችን፣
የአስማተኛ ብልኀት የማይገታቸው እፉኝቶችን እሰድዳለሁ፤
እነርሱም ይነድፏችኋል፤”
ይላል እግዚአብሔር
18በሐዘኔ የምታጽናናኝ#8፥18 የምታጽናናኝ በዕብራይስጡ የዚህ ቃል ትርጕም በግልጽ አይታወቅም። ሆይ፤
ልቤ በውስጤ ዝላለች።
19እንዲህ የሚለውን የሕዝቤን ጩኸት፣
ከሩቅ ምድር ስማ፤
እግዚአብሔር በጽዮን የለምን?
ንጉሧስ በዚያ አይኖርምን?”
“በተቀረጹ ምስሎቻቸው፣
እንዲሁም ከንቱ በሆኑ ባዕዳን ለምን አስቈጡኝ?”
20“መከሩ ዐለፈ፤
በጋው አበቃ፤
እኛም አልዳንም።”
21ሕዝቤ ሲቈስል፣
እኔም ቈሰልሁ፤
አለቀስሁ፤ ድንጋጤ ያዘኝ።
22በገለዓድ የሚቀባ መድኀኒት የለምን?
ወይስ በዚያ ሐኪም አልነበረምን?
ለሕዝቤ ቍስል፣
ለምን ፈውስ አልተገኘም?

Currently Selected:

ኤርምያስ 8: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in