YouVersion Logo
Search Icon

ማቴዎስ 13

13
የዘሪው ምሳሌ
13፥1-15 ተጓ ምብ – ማር 4፥1-12ሉቃ 8፥4-10
13፥16-17 ተጓ ምብ – ሉቃ 10፥23-24
13፥18-23 ተጓ ምብ – ማር 4፥13-20ሉቃ 8፥11-15
1በዚያ ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ አጠገብ ተቀመጠ። 2ብዙ ሕዝብም ስለ ከበበው በባሕሩ ዳር ትቷቸው ጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ። 3ብዙ ነገሮችን በምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “አንድ ገበሬ ዘር ሊዘራ ወጣ። 4ሲዘራም ሳለ፣ አንዳንዱ ዘር መንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው ለቅመው በሉት። 5አንዳንዱም ዘር በቂ ዐፈር በሌለበት በድንጋያማ መሬት ላይ ወደቀ፤ ዐፈሩ ጥልቀት ስላልነበረው ፈጥኖ በቀለ፤ 6ነገር ግን ፀሓይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፤ ሥር ባለመስደዱም ደረቀ። 7ሌላው ዘር በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አደገና ቡቃያውን ዐንቆ አስቀረው፤ 8ሌላውም ዘር ደግሞ በጥሩ መሬት ላይ ወደቀ፤ ፍሬም አፈራ፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ስድሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። 9ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!”
10ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ለምን ለሕዝቡ በምሳሌ ትናገራለህ?” አሉት።
11እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማይን ምስጢር ማወቅ ተሰጥቷችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። 12ላለው ይጨመርለታል፤ ይትረፈረፍለታልም፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። 13ስለዚህ እንዲህ በማለት በምሳሌ የምነግራቸው ለዚህ ነው፤
“እያዩ፣ አያዩም፤
እየሰሙ፣ አይሰሙም ወይም አያስተውሉም፤
14 እንዲህ ተብሎ የተነገረው የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል፤
“ ‘መስማትንስ ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤
ማየትንም ታያላችሁ፤ ነገር ግን ልብ አትሉም።
15 የሕዝቡ ልብ ደንድኗልና፤
ጆሯቸውም አይሰማም፤
እንዳያዩም ዐይናቸውን ጨፍነዋል፤
ይህ ባይሆን ኖሮ፣ በዐይናቸው አይተው፣
በጆሯቸው ሰምተው፣
በልባቸውም አስተውለው፣
ወደ እኔ በተመለሱና በፈወስኋቸው ነበር።’
16 የእናንተ ዐይኖች ስለሚያዩ፣ ጆሮዎቻችሁም ስለሚሰሙ ግን ብፁዓን ናቸው። 17እውነት እላችኋለሁ፤ ብዙ ነቢያትና ብዙ ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ለማየትና የምትሰሙትንም ለመስማት ተመኝተው ነበር፤ ግን አልሆነላቸውም።
18 “እንግዲህ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ፤ 19የእግዚአብሔርን መንግሥት ቃል ሰምቶ ከማያስተውል ከማንኛውም ሰው ልብ ውስጥ ክፉው መጥቶ የተዘራውን ዘር ይነጥቃል። ይህ እንግዲህ በመንገድ ዳር የተዘራው ዘር ነው። 20በጭንጫ መሬት ላይ የተዘራው፣ ቃሉን ሰምቶ ወዲያውኑ በደስታ የሚቀበለውን ሰው ይመስላል። 21ነገር ግን ሥር ባለመስደዱ ብዙ አይቈይም፤ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት ሲመጣ ወዲያውኑ ይሰናከላል። 22በእሾኽ መካከል የተዘራው ዘር ቃሉን ሰምቶ ለዚህ ዓለም በመጨነቅና በብልጽግና ሐሳብ በመታለል ታንቆ ያላፈራን ሰው ይመስላል። 23በጥሩ መሬት ላይ የተዘራው ዘር ግን ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውለውን ሰው ይመስላል፤ በርግጥም ፍሬ ያፈራል፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ስድሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ።”
የእንክርዳዱ ምሳሌ
24ኢየሱስም ሌላ ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ በዕርሻው ቦታ ጥሩ ዘር የዘራን ሰው ትመስላለች። 25ነገር ግን ሰው ሁሉ ተኝቶ ሳለ፣ ጠላቱ መጥቶ በስንዴው መካከል እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። 26ስንዴው በቅሎ ማፍራት ሲጀምር እንክርዳዱም ዐብሮ ብቅ አለ።
27 “የዕርሻው ባለቤት ባሪያዎችም ወደ እርሱ ቀርበው፣ ‘ጌታ ሆይ፤ በዕርሻህ ቦታ ጥሩ ዘር ዘርተህ አልነበረምን? እንክርዳዱ ከየት መጣ?’ አሉት።
28 “እርሱም፣ ‘የጠላት ሥራ ነው’ አላቸው።
“ባሮቹም፣ ‘እንክርዳዱን ሄደን እንድንነቅለው ትፈልጋለህ?’ ብለው ጠየቁት።
29 “እርሱ ግን፣ ‘አይሆንም፤ ምክንያቱም እንክርዳዱን እንነቅላለን ስትሉ ስንዴውንም ዐብራችሁ ልትነቅሉ ትችላላችሁ፤ 30ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ ዐብረው ይደጉ። በዚያ ጊዜ ዐጫጆቹን እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ንቀሉ፤ በእሳትም እንዲቃጠል በየነዶው እሰሩት፤ ስንዴውን ግን ሰብስባችሁ በጐተራዬ ክተቱ እላቸዋለሁ’ አላቸው።”
የሰናፍጭና የእርሾ ምሳሌ
13፥31-32 ተጓ ምብ – ማር 4፥30-32
13፥31-33 ተጓ ምብ – ሉቃ 13፥18-21
31ሌላ ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ አንድ ሰው ወስዶ በዕርሻው ቦታ የዘራትን የሰናፍጭ ዘር ትመስላለች። 32የሰናፍጭ ዘር ከሌሎች ሁሉ ያነሰች ብትሆንም፣ ስታድግ ግን ከአትክልት ሁሉ በልጣ፣ የሰማይ ወፎች መጥተው በቅርንጫፎቿ ላይ እስኪያርፉ ድረስ ዛፍ ትሆናለች።”
33አሁንም ሌላ ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ ሴት ወስዳ ሊጡ በሙሉ እስኪቦካ ድረስ በሦስት መስፈሪያ#13፥33 ምናልባት 27 ኪሎ ግራም ያህል ዱቄት ውስጥ በመደባለቅ የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች።”
34ኢየሱስ ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ተናገረ፤ ምንም ነገር ያለ ምሳሌ አይነግራቸውም ነበር። 35በዚህም በነቢዩ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ተፈጸመ፤
“አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤
ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ።”
የእንክርዳዱ ምሳሌ ትርጕም
36ከዚያም ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው፣ “በዕርሻው ውስጥ ስላለው እንክርዳድ የተናገርኸውን ምሳሌ ትርጕም ንገረን” አሉት።
37እርሱም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ጥሩውን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ 38ዕርሻውም ይህ ዓለም ነው፤ ጥሩው ዘር የእግዚአብሔርን መንግሥት ልጆች ያመለክታል፤ እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፤ 39ዘርቶት የሄደው ጠላትም ዲያብሎስ ነው፤ መከሩ የዓለም መጨረሻ ሲሆን፣ ዐጫጆቹም መላእክት ናቸው።
40 “እንክርዳዱ ተነቅሎ በእሳት እንደሚቃጠል ሁሉ በዓለም መጨረሻም እንዲሁ ይሆናል። 41የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፤ እነርሱም ለኀጢአት ምክንያት የሆኑትንና ክፉ የሚያደርጉትን ሁሉ ለቅመው ከመንግሥቱ ያወጣሉ። 42ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ወደ እቶን እሳት ይጥሏቸዋል። 43በዚያ ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሓይ ያበራሉ። ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ።
የተደበቀ ሀብትና የዕንቍው ምሳሌ
44 “መንግሥተ ሰማይ በዕርሻ ውስጥ የተደበቀ ሀብት ትመስላለች፤ አንድ ሰው ባገኛት ጊዜ መልሶ ሸሸጋት፤ ከመደሰቱም የተነሣ፣ ሄዶ ያለውን ሁሉ በመሸጥ ያን የዕርሻ ቦታ ገዛ።
45 “እንዲሁም መንግሥተ ሰማይ ውብ ዕንቍ የሚፈልግ ነጋዴ ትመስላለች፤ 46እጅግ ውድ የሆነ ዕንቍ ባገኘም ጊዜ፣ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጦ ገዛው።
የመረቡ ምሳሌ
47 “ደግሞም መንግሥተ ሰማይ ወደ ባሕር ተጥሎ የዓሣ ዐይነቶችን የያዘ መረብ ትመስላለች፤ 48ዓሣ አጥማጆቹ መረቡ ሲሞላላቸው ጐትተው ወደ ባሕሩ ዳር አወጡት፤ ከዚያም ተቀምጠው ጥሩ ጥሩውን እየለዩ በቅርጫት ውስጥ ጨመሩ፤ መጥፎ መጥፎውን ግን ጣሉት። 49በዓለም መጨረሻም ልክ እንደዚሁ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ኀጢአተኞችን ከጻድቃን በመለየት፣ 50ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ወደ እቶን እሳት ይጥሏቸዋል።”
51ኢየሱስ፣ “ይህ ሁሉ ገብቷችኋል?” አላቸው።
እነርሱም፣ “አዎን” አሉት።
52እርሱም፣ “ስለዚህም የመንግሥተ ሰማይን ምስጢር የተረዳ ማንኛውም የኦሪት ሕግ መምህር፣ ከከበረ ሀብቱ ክምችት አዲሱንም አሮጌውንም የሚያወጣ ባለንብረት ይመስላል” አላቸው።
በገዛ አገሩ ያልተከበረው ነቢይ
13፥54-58 ተጓ ምብ – ማር 6፥1-6
53ኢየሱስ እነዚህን ምሳሌዎች እንደ ጨረሰ፣ ከዚያ ስፍራ ተነሥቶ ሄደ፤ 54ወደ ገዛ አገሩ መጣ፤ በምኵራባቸውም ሕዝቡን ያስተምር ጀመር። እነርሱም በመገረም እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሰው ይህን ጥበብና እነዚህን ታምራት የማድረግ ኀይል ከየት አገኘ? 55ይህ የዐናጺው ልጅ አይደለምን? የእናቱስ ስም ማርያም አይደለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብ፣ ዮሴፍ፣ ስምዖንና ይሁዳ አይደሉምን? 56እኅቶቹስ ከእኛው ጋራ አይደሉምን? ታዲያ ይህ ሰው ይህን ሁሉ ከወዴት አገኘው?” 57ከዚህም የተነሣ ተሰናከሉበት።
ኢየሱስ ግን፣ “ነቢይ የማይከበረው በራሱ አገርና በራሱ ቤት ብቻ ነው” አላቸው።
58ባለማመናቸውም ምክንያት ብዙ ታምራትን በዚያ አላደረገም።

Currently Selected:

ማቴዎስ 13: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in