ማቴዎስ 16
16
ኢየሱስ ከሰማይ ምልክት እንዲያሳይ መጠየቁ
16፥1-12 ተጓ ምብ – ማር 8፥11-21
1ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ወደ ኢየሱስ ቀርበው ሊፈትኑት ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት።
2እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤#16፥2 አንዳንድ የጥንት ቅጆች የቍጥር 2 ከፊልና ቍጥር 3 በሙሉ የላቸውም። “ምሽት ላይ፣ ‘ሰማዩ ስለ ቀላ ብራ ይሆናል’ ትላላችሁ፤ 3ንጋት ላይም፣ ‘ሰማዩ ቀልቷል፣ ከብዷልም፤ ስለዚህ ዝናብ ይዘንባል’ ትላላችሁ። የሰማዩን ገጽታ ትለያላችሁ፤ ነገር ግን የዘመኑን ምልክት መለየት አትችሉም። 4ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ከዮናስ ምልክት በቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም።” ከዚያም ኢየሱስ ትቷቸው ሄደ።
የፈሪሳውያንና የሰዱቃውያን እርሾ
5ባሕሩን እንደ ተሻገሩም፣ ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ረስተው ነበር። 6ኢየሱስም፣ “ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠበቁ” አላቸው።
7እነርሱም እርስ በርሳቸው፣ “እንጀራ ስላልያዝን ነው” ተባባሉ።
8ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ እምነት የጐደላችሁ፤ እርስ በርሳችሁ፣ እንጀራ ስለሌለን ነው በማለት የምትነጋገሩት ስለ ምንድን ነው? 9ዐምስቱ እንጀራ ለዐምስት ሺሕ ሰው በቅቶ ስንት መሶብ ተርፎ እንዳነሣችሁ አታስታውሱምን? 10እንዲሁም ሰባቱ እንጀራ ለአራት ሺሕ ሰው በቅቶ ስንት መሶብ ተርፎ እንዳነሣችሁ ልብ አላላችሁም ማለት ነውን? 11ታዲያ የነገርኋችሁ ስለ እንጀራ እንዳልሆነ እንዴት አታስተውሉም? አሁንም ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ።” 12በዚህ ጊዜ ያስጠነቀቃቸው እንጀራ ውስጥ ስለሚጨመረው እርሾ ሳይሆን፣ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት መሆኑ ገባቸው።
ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ ማንነት መናገሩ
16፥13-16 ተጓ ምብ – ማር 8፥27-29፤ ሉቃ 9፥18-20
13ኢየሱስ ፊልጶስ ቂሳርያ ወደተባለው ግዛት በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ለመሆኑ ሰዎች፣ የሰውን ልጅ ማን ነው ይላሉ?” ብሎ ጠየቃቸው።
14እነርሱም፣ “አንዳንዶቹ መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎች ኤልያስ፣ ሌሎች ደግሞ ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” አሉት።
15እርሱም፣ “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው።
16ስምዖን ጴጥሮስም፣ “አንተ ክርስቶስ#16፥16 በግሪኩ ክርስቶስ፣ በዕብራይስጡ መሲሕ የሁለቱም ቃላት ትርጕም የተቀባው ማለት ነው። የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” በማለት መለሰ።
17ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፣ ምስጉን ነህ፤ ይህን የገለጠልህ በሰማይ ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም አይደለም። 18አንተ ጴጥሮስ#16፥18 ጴጥሮስ ትርጕሙ ዐለት ማለት ነው። ነህ፤ በዚህ ዐለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አያሸንፏትም።#16፥18 ወይም ሊቋቋሟት አይችሉም 19የመንግሥተ ሰማይን መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር ያሰርኸው ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የፈታኸው ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል።” 20ቀጥሎም እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ለማንም እንዳይናገሩ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው።
ኢየሱስ ስለሚደርስበት መከራ ተናገረ
16፥21-28 ተጓ ምብ – ማር 8፥31–9፥1፤ ሉቃ 9፥22-27
21ኢየሱስ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ፣ በዚያም በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት እጅ መከራን ይቀበልና ይገደል ዘንድ፣ በሦስተኛው ቀን ከሞት ይነሣ ዘንድ እንደሚገባው ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጽላቸው ጀመር።
22ጴጥሮስም ኢየሱስን ወደ ጐን ሳብ አድርጎ፣ “ጌታ ሆይ፤ እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይድረስብህ” እያለ ይገሥጸው ጀመር።
23ኢየሱስም ወደ ጴጥሮስ ዘወር ብሎ፣ “አንተ ሰይጣን፤ ወደ ኋላዬ ሂድ! የሰው እንጂ የእግዚአብሔር ነገር በሐሳብህ ስለሌለ መሰናክል ሆነህብኛል” አለው።
24ከዚያም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ “ሊከተለኝ የሚወድድ ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ፤ 25ነፍሱን#16፥25 የግሪኩ ቃል ትርጕም ሕይወት ወይም ነፍስ ነው፤ እንደዚሁም 26። ሊያድን የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፤ ነገር ግን ነፍሱን ስለ እኔ የሚያጠፋት ያድናታል። 26ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ፣ ነፍሱን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው በነፍሱ ምትክ ሊከፍለው የሚችለው ዋጋ ምንድን ነው? 27የሰው ልጅ በአባቱ ክብር ከመላእክት ጋራ ይመጣል፤ ለእያንዳንዱም ሰው እንደ ሥራው ዋጋውን ይከፍለዋል። 28እውነት እላችኋለሁ፣ እዚህ ከቆሙት ሰዎች መካከል፣ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስከሚያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አሉ።”
Currently Selected:
ማቴዎስ 16: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.