ምሳሌ 2
2
ከጥበብ የሚገኝ በረከት
1ልጄ ሆይ፤ ቃሌን ብትቀበል፣
ትእዛዜንም በልብህ ብታኖር፣
2ጆሮህን ወደ ጥበብ ብታቀና፣
ልብህንም ወደ ማስተዋል ብትመልስ፣
3እንዲሁም የመለየት ጥበብን ብትማጠን፣
ድምፅህን ከፍ አድርገህ ማስተዋልን ብትጣራ፣
4እርሷንም እንደ ብር ብትፈልጋት፣
እንደ ተሸሸገ ሀብት አጥብቀህ ብትሻት፣
5በዚያን ጊዜ ፈሪሀ እግዚአብሔርን ትረዳለህ፤
አምላክንም ማወቅ ታገኛለህ።
6 እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤
ከአንደበቱም ዕውቀትና ማስተዋል ይወጣል።
7እርሱ ለቅኖች ድልን ያከማቻል፤
ያለ ነቀፋ ለሚሄዱትም ጋሻ ይሆናቸዋል፤
8የፍትሕን መንገድ ይጠብቃል፤
የታማኞቹንም አካሄድ ያጸናል።
9በዚያን ጊዜ ጽድቅን፣ ፍትሕን፣ ሚዛናዊነትን፣
መልካሙንም መንገድ ሁሉ ትገነዘባለህ፤
10ጥበብ ልብህ ውስጥ ትገባለችና፤
ዕውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለች፤
11የመለየት ችሎታ ይጋርድሃል፤
ማስተዋልም ይጠብቅሃል።
12ጥበብ ንግግራቸው ጠማማ ከሆነ ሰዎች፣
ከክፉዎችም መንገድ ታድንሃለች፤
13እነዚህም በጨለማ መንገድ ለመሄድ፣
ቀናውን ጐዳና የሚተዉ ናቸው፤
14ክፉ በመሥራት ደስ የሚላቸው፣
በክፋት ጐዳና ሐሤት የሚያደርጉ፣
15መንገዳቸው ጠማማ፣
በአካሄዳቸው ጠመዝማዞች ናቸው።
16ከአመንዝራ ሴትም ትጠብቅሃለች፤
በአንደበቷም ከምታታልል ዘልዛላ ታድንሃለች፤
17ይህችም የልጅነት ባሏን የተወች፣
በአምላኳ ፊት የገባችውን ኪዳን#2፥17 ወይም የአምላኳን ኪዳን ያቃለለች ናት።
18ቤቷ ወደ ሞት ያደርሳል፤
መንገዷም ወደ መናፍስተ ሙታን ያመራል።
19ወደ እርሷ የሚገባ ማንም አይመለስም፤
የሕይወትንም መንገድ አያገኝም።
20አንተም በደጋግ ሰዎች ጐዳና ትሄዳለህ፤
የጻድቃንንም መንገድ ይዘህ ትጓዛለህ።
21ቅኖች በምድሪቱ ይቀመጣሉና፤
ነቀፋ የሌለባቸውም በእርሷ ላይ ጸንተው ይኖራሉ።
22ክፉዎች ግን ከምድሪቱ ይወገዳሉ፤
ታማኝነት የጐደላቸውም ከእርሷ ይነቀላሉ።
Currently Selected:
ምሳሌ 2: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.