መዝሙር 25
25
መዝሙር 25#25 ይህ መዝሙር እያንዳንዱ ጥቅስ ተከታታይ ፊደላት ባሉት የዕብራይስጥ ሆህያት የሚጀምር፣ ጅማሬው ወይም ጅማሬውና መጨረሻው ትርጕም የሚሰጥ ግጥም ነው።
የዳዊት መዝሙር።
1 እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤
ነፍሴን ወደ አንተ አነሣለሁ።
2አምላኬ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ፤
እባክህ አታሳፍረኝ፤
ጠላቶቼም አይዘባነኑብኝ።
3አንተን ተስፋ የሚያደርጉ፣
ከቶ አያፍሩም፤
ነገር ግን እንዲያው ያለ ምክንያት፣
ተንኰለኞች የሆኑ ያፍራሉ።
4 እግዚአብሔር ሆይ፤ አካሄድህን እንዳውቅ አድርገኝ፤
መንገድህንም አስተምረኝ።
5አንተ አዳኜ፣ አምላኬም ነህና፣
በእውነትህ ምራኝ፤ አስተምረኝም፤
ቀኑን ሙሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ።
6 እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህንና ፍቅርህን ዐስብ፤
እነዚህ ከጥንት የነበሩ ናቸውና።
7የልጅነቴን ኀጢአት፣
መተላለፌንም አታስብብኝ፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቸርነትህ ብዛት፣
እንደ ምሕረትህም መጠን አስበኝ።
8 እግዚአብሔር መልካምና ቅን ነው፤
ስለዚህ ኀጢአተኞችን በመንገድ ይመራቸዋል።
9ዝቅ ያሉትን በፍትሕ ይመራቸዋል፤
ለትሑታንም መንገዱን ያስተምራቸዋል።
10ኪዳኑንና ምስክርነቱን ለሚጠብቁ፣
የእግዚአብሔር መንገድ ሁሉ ቸርነትና እውነት ናቸው።
11 እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀጢአቴ ታላቅ ነውና፣
ስለ ስምህ ይቅር በልልኝ።
12 እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ማን ነው?
በተመረጠለት መንገድ ያስተምረዋል።
13ዘመኑን በተድላ ደስታ ያሳልፋል፤
ዘሩም ምድርን ይወርሳል።
14 እግዚአብሔር ምስጢሩን ከሚፈሩት ወዳጆቹ አይሰውርም፤
ኪዳኑንም ይገልጥላቸዋል።
15ዐይኖቼ ሁልጊዜ ወደ እግዚአብሔር ናቸው፤
እግሮቼን ከወጥመድ የሚያላቅቃቸው እርሱ ነውና።
16እኔ ብቸኛና የተጨነቅሁ እንደ መሆኔ፣
ወደ እኔ ተመለስ፤ ምሕረትም አድርግልኝ።
17የልቤ መከራ በዝቷል፤
ከጭንቀቴ ገላግለኝ።
18ጭንቀቴንና መከራዬን ተመልከት፤
ኀጢአቴንም ሁሉ ይቅር በለኝ።
19ጠላቶቼ እንዴት እንደ በዙ ተመልከት፤
እንዴት አምርረው እንደሚጠሉኝ እይ።
20ነፍሴን ጠብቃት፤ ታደገኝም፤
መጠጊያዬ ነህና አታሳፍረኝ።
21አንተን ተስፋ አድርጌአለሁና፣
ታማኝነትና ቅንነት ይጠብቁኝ።
22አምላክ ሆይ፤ እስራኤልን
ከመከራው ሁሉ አድነው።
Currently Selected:
መዝሙር 25: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.