ራእይ 3
3
በሰርዴስ ላለው ቤተ ክርስቲያን
1 “በሰርዴስ ላለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ # 3፥1 ለቍጥር 7 እና 14 ወይም መልእክተኛ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤
ሰባቱን የእግዚአብሔር መናፍስትና # 3፥1 ወይም ሰባት ዕጥፍ መንፈስ ሰባቱን ከዋክብት በእጁ የያዘው እንዲህ ይላል።
ሥራህን ዐውቃለሁ፤ በስም ሕያው ነህ፤ ነገር ግን ሞተሃል። 2ስለዚህ ንቃ፤ ሊሞት የተቃረበውን የቀረውን ነገር አጽና፤ ሥራህ በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትም። 3እንግዲህ የተቀበልኸውንና የሰማኸውን አስታውስ፤ ታዘዘውም፤ ንስሓም ግባ። ባትነቃ ግን እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ፤ በየትኛው ሰዓት እንደምመጣብህም አታውቅም።
4 ነገር ግን ልብሳቸውን ያላሳደፉ ጥቂት ሰዎች በሰርዴስ ከአንተ ጋራ አሉ፤ እነርሱም ነጭ ልብስ ለብሰው ከእኔ ጋራ ይሄዳሉ፤ ይህ የሚገባቸው ነውና። 5ድል የሚነሣም እንደ እነርሱ ነጭ ልብስ ይለብሳል፤ እኔም በአባቴና በመላእክቱ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም። 6መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።
በፊላድልፍያ ላለው ቤተ ክርስቲያን
7 “በፊላድልፍያ ላለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤
ቅዱስና እውነተኛ የሆነው፣ የዳዊትንም መክፈቻ በእጁ የያዘው እንዲህ ይላል፤ እርሱ የከፈተውን ማንም ሊዘጋው አይችልም፤ የዘጋውንም ማንም ሊከፍተው አይችልም።
8 ሥራህን ዐውቃለሁ። እነሆ፤ ማንም ሊዘጋው የማይችል የተከፈተ በር በፊትህ አድርጌአለሁ። ኀይልህ ትንሽ እንደ ሆነ ዐውቃለሁ፤ ሆኖም ቃሌን ጠብቀሃል፤ ስሜንም አልካድህም። 9እነሆ፣ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን የሚሉት፣ የሚዋሹት፣ የሰይጣን ማኅበር የሆኑት ወደ አንተ እንዲመጡ በእግርህ ሥር እንዲሰግዱ፣ እኔ እንደ ወደድሁህም እንዲያውቁ አደርጋለሁ። 10በትዕግሥት እንድትጸና የሰጠሁህን ትእዛዜን ስለ ጠበቅህ፣ እኔ ደግሞ በምድር ላይ የሚኖሩትን ሊፈትናቸው በዓለም ሁሉ ላይ ከሚመጣው የፈተና ሰዓት እጠብቅሃለሁ።
11 ቶሎ እመጣለሁ፤ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጥብቀህ ያዝ። 12ድል የሚነሣውን በአምላኬ ቤተ መቅደስ ውስጥ ዐምድ አደርገዋለሁ፤ ከዚያም ከቶ አይወጣም። የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም ይኸውም ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን የአዲሲቱን ኢየሩሳሌም ስም በርሱ ላይ እጽፋለሁ፤ አዲሱን ስሜንም በርሱ ላይ እጽፋለሁ። 13መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።
በሎዶቅያ ላለው ቤተ ክርስቲያን
14 “በሎዶቅያ ላለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤
አሜን የሆነው፣ ደግሞም ታማኝና እውነተኛ ምስክር የሆነው፣ የእግዚአብሔርም ፍጥረት ምንጭ # 3፥14 ገዥ ወይም ጀማሪ የሆነው እንዲህ ይላል።
15 ቀዝቃዛ ወይም ትኵስ እንዳልሆንህ ሥራህን ዐውቃለሁ፤ ቀዝቃዛ ወይም ትኵስ ብትሆን በወደድሁ ነበር። 16እንግዲህ ለብ ያልህ ብቻ እንጂ ትኵስ ወይም ቀዝቃዛ ስላልሆንህ ከአፌ አውጥቼ ልተፋህ ነው። 17‘ሀብታም ነኝ፣ ባለጠጋ ነኝ፣ አንዳችም አያስፈልገኝም’ ትላለህ፤ ነገር ግን ጐስቋላ፣ ምስኪን፣ ድኻ፣ ዕውርና የተራቈትህ መሆንህን አታውቅም። 18ስለዚህ ሀብታም እንድትሆን፣ በእሳት የነጠረ ወርቅ እንድትገዛ፣ የዕራቍትነትህ ኀፍረት እንዳይታይ፣ ነጭ ልብስ እንድትለብስና ለማየት እንድትችል ዐይንህን በኵል እንድትኳል እመክርሃለሁ።
19 እኔ የምወድዳቸውን እገሥጻለሁ፤ እቀጣለሁም። ስለዚህ ትጋ፤ ንስሓም ግባ። 20እነሆ፤ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ሰምቶ በሩን ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ ገብቼ ከርሱ ጋራ እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋራ ይበላል።
21 እኔ ድል ነሥቼ ከአባቴ ጋራ በርሱ ዙፋን ላይ እንደ ተቀመጥሁ፣ ድል የሚነሣውንም ከእኔ ጋራ በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ። 22መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።”
Currently Selected:
ራእይ 3: NASV
Highlight
Share
Copy

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.