ቲቶ 2
2
ስለ ወንጌል መልካምን ስለ ማድረግ
1አንተ ግን ከትክክለኛው ትምህርት ጋራ ተስማሚ የሆነውን አስተምር። 2አረጋውያን ጭምቶች፣ የተከበሩ፣ ራሳቸውን የሚገዙና በእምነት፣ በፍቅርና በትዕግሥት ጤናማነት ያላቸው እንዲሆኑ ምከራቸው።
3እንዲሁም አሮጊቶች በአኗኗራቸው የተከበሩ እንዲሆኑ፣ በጎ የሆነውን የሚያስተምሩ እንጂ የሰው ስም የሚያጠፉ ወይም በወይን ጠጅ ሱስ የተጠመዱ እንዳይሆኑ አስተምራቸው። 4እንዲህ ከሆኑ፣ ወጣት ሴቶች ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን እንዲወድዱ ማስተማር ይችላሉ፤ 5የእግዚአብሔር ቃል በማንም ዘንድ እንዳይሰደብ ራሳቸውን የሚገዙና ንጹሓን፣ በቤት ውስጥ በሥራ የተጠመዱ፣ ቸሮች፣ ለባሎቻቸው የሚገዙ እንዲሆኑ ያስተምሯቸው።
6እንዲሁም ወጣት ወንዶች ራሳቸውን እንዲገዙ ምከራቸው። 7በማንኛውም ነገር መልካም የሆነውን ነገር በማድረግ ራስህን አርኣያ አድርገህ አቅርብላቸው። በምታስተምራቸውም ትምህርት ጭምተኛነትን፣ ቁም ነገረኛነትን፣ 8የማይነቀፍ ጤናማ አነጋገርንም አሳይ፤ ይኸውም ተቃዋሚ ስለ እኛ የሚናገረውን መጥፎ ነገር በማጣት እንዲያፍር ነው።
9ባሮች ለጌቶቻቸው በማንኛውም ነገር እንዲገዙ፣ ደስ እንዲያሰኟቸውና የዐጸፋ ቃል እንዳይመልሱላቸው አስተምር፤ 10አይስረቁ፤ ይኸውም በሁሉም መንገድ የአዳኛችን የእግዚአብሔር ትምህርት ይወደድ ዘንድ ፍጹም ታማኝ መሆናቸውን እንዲያስመሰክሩ ነው።
11ድነት የሚገኝበት የእግዚአብሔር ጸጋ ለሰዎች ሁሉ ተገልጧልና፤ 12ይህም ጸጋ በኀጢአት መኖርንና ዓለማዊ ምኞትን ክደን፣ በአሁኑ ዘመን ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ፣ በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት እንድንኖር ያስተምረናል#2፥12 ያሠለጥነናል ተብሎ ሊተረጐም ይችላል።፤ 13ይህም የተባረከ ተስፋችን የሆነውን የታላቁን የአምላካችንንና የአዳኛችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ በመጠባበቅ ነው፤ 14እርሱም ከክፋት ሊቤዠን፣ መልካም የሆነውን ለማድረግ የሚተጋውን የርሱ የሆነውን ሕዝብም ለራሱ ያነጻ ዘንድ ራሱን ስለ እኛ ሰጥቷል።
15እንግዲህ ልታስተምር የሚገባህ እነዚህን ነው፤ በሙሉ ሥልጣን ምከር፤ ገሥጽም፤ ማንም አይናቅህ።
Currently Selected:
ቲቶ 2: NASV
Highlight
Share
Copy
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fen.png&w=128&q=75)
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.