YouVersion Logo
Search Icon

1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 12

12
የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች
1ወንድሞቼ ሆይ! አሁን ደግሞ ስለ መንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች እንድታውቁ እፈልጋለሁ። 2አሕዛብ በነበራችሁበት ጊዜ በማታውቁት ነገር ተመርታችሁ መናገር ወደማይችሉ ጣዖቶች ትወሰዱ እንደ ነበር ታውቃላችሁ። 3ስለዚህ በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርቶ ኢየሱስን የሚረግም ማንም የለም፤ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ካልሆነ በቀር “ኢየሱስ ጌታ ነው!” የሚል ማንም እንደሌለ እነግራችኋለሁ።
4ልዩ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች አሉ፤ መንፈስ ቅዱስ ግን አንድ ነው። 5ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ፤ ጌታ ግን አንድ ነው። 6ልዩ ልዩ የሥራ ዐይነቶችም አሉ፤ ነገር ግን ሁሉንም በሁሉ የሚያከናውን አንዱ እግዚአብሔር ነው። 7ለእያንዳንዱ መንፈስ ቅዱስን የመግለጥ ስጦታ የሚሰጠው ለጋራ ጥቅም ነው። 8መንፈስ ቅዱስ ለአንዱ ሰው በጥበብ የመናገር ችሎታን ይሰጠዋል፤ ለሌላው ሰው ደግሞ ያው መንፈስ በዕውቀት የመናገርን ችሎታ ይሰጠዋል፤ 9ያው አንዱ መንፈስ ለአንዱ እምነትን ይሰጠዋል፤ ለሌላውም የመፈወስ ስጦታን ይሰጠዋል፤ 10እንዲሁም ለአንዱ ተአምራትን የማድረግ ኀይል ይሰጠዋል፤ ለሌላው የትንቢትን ቃል የመናገር ችሎታ ይሰጠዋል፤ ለሌላው ደግሞ ስጦታዎች ከመንፈስ ቅዱስ መሆናቸውን ወይም ከርኩሳን መናፍስት መሆናቸውን ለይቶ የማወቅ ችሎታን ይሰጠዋል፤ እንዲሁም ለአንዱ በተለያዩ ቋንቋዎች የመናገር ችሎታን ይሰጠዋል፤ ለሌላው ደግሞ በተለያዩ ቋንቋዎች የተነገረውን የመተርጐም ችሎታን ይሰጠዋል፤ #12፥10 የትንቢት ቃል፦ የእግዚአብሔርን ቃል መተርጐም ወይም ማብራራት ነው። (ሮሜ 12፥6 ተመልከት) 11ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ የሚያደርገው ያው አንዱ መንፈስ ቅዱስ ነው፤ መንፈስ ቅዱስ እንደ ፈቀደ ለእያንዳንዱ ሰው የተለየ ስጦታን ይሰጠዋል። #ሮም 12፥6-8።
በአንድ ሰው አካል የተለያዩ ክፍሎች መኖራቸው
12አንድ ሰው ብዙ የአካል ክፍሎች አሉት፤ የአካል ክፍሎች ብዙዎች ሆነው ሳሉ የሚገኙት በዚያው በአንዱ አካል ነው። እንዲሁም ክርስቶስ ብዙ የሰውነት ክፍሎች እንዳሉት እንደ አንድ አካል ነው። #ሮም 12፥4-5። 13አይሁድም ብንሆን የግሪክ ሰዎች ብንሆን፤ ባሪያዎችም ብንሆን፥ ነጻ ሰዎችም ብንሆን፥ አንድ ሰውነት ለመሆን በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቀናል፤ ሁላችንም ከዚሁ ከአንዱ መንፈስ ጠጥተናል።
14አንድ አካል የተሠራው ከብዙ የአካል ክፍሎች እንጂ ከአንድ የአካል ክፍል ብቻ አይደለም! 15እግር “እኔ እጅ ስላልሆንኩ የአካል ክፍል አይደለሁም!” ቢል ታዲያ እንዲህ በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን? 16ጆሮም “እኔ ዐይን ስላልሆንኩ የአካል ክፍል አይደለሁም” ቢል፥ ታዲያ፥ እንዲህ በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን? 17አንድ አካል በሙሉ ዐይን ብቻ ቢሆን ኖሮ በምን መስማት ይቻል ነበር? አንድ አካል በሙሉ ጆሮ ብቻ ቢሆን ኖሮ በምን ማሽተት ይቻል ነበር? 18አሁን ግን እግዚአብሔር እንደ ፈለገው እያንዳንዱን የአካል ክፍል በአካል ውስጥ ተገቢ ስፍራውን ይዞ እንዲገኝ አድርጎታል። 19ሁላቸውም አንድ ክፍል ብቻ ቢሆን ኖሮ ሙሉ አካል የት በተገኘ ነበር! 20አሁን ግን ብዙ የአካል ክፍሎች ቢኖሩም አካል ግን አንድ ብቻ ነው።
21ዐይን እጅን “አንተ አታስፈልገኝም!” ሊለው አይችልም፤ ራስም እግርን “አንተ አታስፈልገኝም!” ሊለው አይችልም፤ 22እንዲያውም በጣም ደካሞች መስለው የሚታዩ የአካል ክፍሎች ይበልጥ አስፈላጊ ናቸው። 23አነስተኛ ክብር ያላቸው መስለው ለሚታዩን የአካል ክፍሎች ይበልጥ ክብር እንሰጣቸዋለን፤ ለማየት የሚያሳፍሩ መስለው ለሚታዩን የሰውነት ክፍሎች ይበልጥ ክብር ሰጥተን እንጠነቀቅላቸዋለን፤ 24ፊት ለፊት ለሚታዩት የአካል ክፍሎች ግን ይህ ሁሉ አያስፈልጋቸውም፤ እግዚአብሔር ግን ለማየት የሚያሳፍሩ መስለው የሚታዩንን የአካል ክፍሎች በበለጠ ክብር እንዲያዙ አድርጎ የአካል ክፍሎችን አገጣጥሞአል። 25ይህንንም ያደረገው በአካል ክፍሎች መካከል መለያየት ሳይኖር እርስ በርሳቸው እንዲተሳሰቡ ነው። 26አንዱ የአካል ክፍል ሲሠቃይ ሌሎችም የአካል ክፍሎች በሙሉ አብረው ይሠቃያሉ፤ አንዱ የሰውነት ክፍል ሲከበር ሌሎቹም የሰውነት ክፍሎች አብረው ከእርሱ ጋር ይደሰታሉ።
27እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁም የአካሉ ክፍሎች ናችሁ። 28ስለዚህ እግዚአብሔር እያንዳንዱ ሰው በቤተ ክርስቲያን የተለያየ አገልግሎት እንዲኖረው አድርጓል፤ በዚህም መሠረት በመጀመሪያ ሐዋርያትን፥ ሁለተኛ ነቢያትን፥ ሦስተኛ መምህራንን ሾሞአል። ቀጥሎም ተአምራት የሚያደርጉትን፥ ቀጥሎም የመፈወስ ስጦታ ያላቸውን፥ ሰዎችን የመርዳት ስጦታ ያላቸውን፥ አስተዳዳሪዎችንና በተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩትን ሰዎች መድቦአል። #ኤፌ. 4፥11። 29ሁሉም ሐዋርያት ናቸውን? ሁሉም ነቢያት ናቸውን? ሁሉም መምህራን ናቸውን? ሁሉም ተአምራት የሚያደርጉ ናቸውን? 30ሁሉም የመፈወስ ስጦታ አላቸውን? ሁሉም በተለያዩ ቋንቋዎች የመናገር ችሎታ አላቸውን? ሁሉም በተለያዩ ቋንቋዎች የተነገረውን የመተርጐም ችሎታ አላቸውን? 31ስለዚህ በጣም የሚበልጡትን ስጦታዎች ለማግኘት ፈልጉ።
አሁን ደግሞ ከሁሉ የሚበልጠውን መንገድ አሳያችኋለሁ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in