1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13
13
እውነተኛ ፍቅር
1በሰዎችም ሆነ በመላእክት ቋንቋ የመናገር ችሎታ ቢኖረኝ እንኳ ፍቅር ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሿሿ ጸናጽል መሆኔ ነው። 2ትንቢት የመናገር ስጦታ ቢኖረኝና ምሥጢርንም ሁሉ ብረዳ፥ ዕውቀትም ሁሉ ቢኖረኝ፥ ተራራን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚያፈልስ እምነትም ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። #ማቴ. 17፥20፤ 21፥21፤ ማር. 11፥23። 3ያለኝን ሁሉ ለድኾች ባካፍል፥ ሥጋዬም እንኳ ሳይቀር በእሳት እንዲቃጠል አሳልፌ ብሰጥ፥ ፍቅር ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። #13፥3 በእሳት እንዲቃጠል፦ አንዳንድ የብራና ጽሑፎች “ለትምክሕት” ይላሉ።
4ፍቅር ያስታግሣል፤ ፍቅር ደግ ያደርጋል፤ ፍቅር ቀናተኛ አያደርግም፤ ፍቅር ያለው ሰው አይመካም፤ ፍቅር ያለው ሰው አይታበይም፤ 5ፍቅር ሥርዓተቢስ አያደርግም፤ ፍቅር ያለው ሰው የራሱን ጥቅም ብቻ አይፈልግም፤ ፍቅር ያለው ሰው አይበሳጭም፤ ፍቅር ያለው ሰው ቢበደልም በደልን እንደ በደል አይቈጥርም፤ 6ፍቅር ያለው ሰው እውነት በሆነ ነገር ይደሰታል እንጂ ትክክል ባልሆነ ነገር አይደሰትም፤ 7ፍቅር ያለው ሰው ሁሉን ይችላል፤ በሁሉም ላይ እምነቱን ይጥላል፤ በሁሉም ላይ ተስፋ ያደርጋል፤ በሁሉ ነገር ይጸናል።
8ፍቅር ያለው ሰው ምንጊዜም አይወድቅም፤ ትንቢትን የመናገር ስጦታ ያልፋል፤ በተለያዩ ቋንቋዎች የመናገር ችሎታ ያልፋል፤ ዕውቀትም ቢሆን ያልፋል። 9የምናውቀውም ሆነ ትንቢት የምንናገረው በከፊል ነው። 10ነገር ግን ፍጹም የሆነው ነገር ሲመጣ ከፊል የሆነው ነገር ይሻራል።
11ሕፃን በነበርኩ ጊዜ እንደ ሕፃን እናገር ነበር፤ እንደ ሕፃን አስብ ነበር፤ እንደ ሕፃን እመራመር ነበር፤ ሙሉ ሰው በሆንኩ ጊዜ ግን የሕፃንነቴን ጠባይ ተውኩ። 12አሁን በመስተዋት እንደምናየው ዐይነት በድንግዝግዝ እናያለን፤ በዚያን ጊዜ ግን በግልጥ እናያለን፤ አሁን የማውቀው በከፊል ነው፤ በዚያን ጊዜ ግን እግዚአብሔር እኔን የሚያውቀኝን ያኽል ሙሉ ዕውቀት ይኖረኛል።
13እንግዲህ እምነት፥ ተስፋ፥ ፍቅር፥ እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ነገር ግን ከእነዚህ መካከል የሚበልጠው ፍቅር ነው።
Currently Selected:
1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997