1 የጴጥሮስ መልእክት 1
1
1የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነው ከጴጥሮስ፥
መጻተኞች ሆናችሁ በጳንጦስ፥ በገላትያ፥ በቀጰዶቅያ፥ በእስያ፥ በቢታንያ ተበታትናችሁ ለምትኖሩት 2እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ በዐቀደው መሠረት ለተመረጣችሁት፥ ለኢየሱስ ክርስቶስ ለመታዘዝና በደሙ ተረጭታችሁ ለመንጻት በመንፈስ ቅዱስ ለተቀደሳችሁት፥
ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።
ሕያው ተስፋ
3ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ምክንያት ሕያው የሆነውን ተስፋ የሰጠን፥ በታላቅ ምሕረቱ በአዲስ ልደት ልጆቹ ያደረገን፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን፤ 4እርሱም የማይጠፋውን፥ የማይበላሸውንና የማያረጀውን ርስት በሰማይ አዘጋጅቶላችኋል። 5እናንተም በመጨረሻው ቀን ለሚገለጠው መዳን በእምነት አማካይነት በእግዚአብሔር ኀይል ተጠብቃችኋል። 6ምንም እንኳ የተለያዩ ፈተናዎች ለጥቂት ጊዜ የሚያስቸግሩአችሁ ቢሆኑ በእርሱ ደስ ይበላችሁ። 7ይህ ፈተና የሚደርስባችሁ የእምነታችሁን እውነተኛነት ለማረጋገጥ ነው፤ የሚጠፋ ወርቅ እንኳ በእሳት ይፈተናል፤ ከወርቅ ይልቅ የከበረ እምነታችሁ እንደዚሁ መፈተን አለበት፤ ይህም የተፈተነ እምነታችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ምስጋናን፥ ክብርንና ውዳሴን ያስገኝላችኋል። 8ኢየሱስ ክርስቶስን ያላያችሁት እንኳ ብትሆኑ ትወዱታላችሁ፤ አሁን እንኳ የማታዩት ብትሆኑ ታምኑበታላችሁ፤ በቃላት ሊገለጥ በማይቻልና በከበረ ደስታ ደስ ይላችኋል። 9በእምነታችሁም የምትጠብቁትን የነፍሳችሁን መዳን ታገኛላችሁ።
10ስለዚህ መዳን ጉዳይ የእናንተ ስለሚሆነው ጸጋ የተነበዩት ነቢያት ጥልቅ ምርምርና ጥናት አድርገዋል። 11ከእነርሱ ውስጥ የነበረውም የክርስቶስ መንፈስ በመሲሑ ላይ ስለሚደርሰው መከራና ከመከራውም በኋላ ስለሚያገኘው ክብር አስቀድሞ አመልክቶ ነበር፤ እነርሱም ይህ ሁሉ በምን ጊዜና በእንዴት ያለ ሁኔታ እንደሚሆን መርምረው ነበር፤ 12እነዚህ ነቢያት ያገለግሉ የነበሩት እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳልነበረ ተገልጦላቸዋል፤ ያገለገሉአችሁም ከሰማይ በተላከው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት አሁን ወንጌልን ያበሠሩአችሁ ሰዎች የነገሩአችሁን በመግለጥ ነው፤ ይህን ነገር መላእክት እንኳ ለማየት ይመኙት ነበር።
በቅድስና ስለመኖር
13ስለዚህ ልቡናችሁን አንቅታችሁ ለሥራ ተዘጋጁ፤ በመጠን ኑሩ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ለምታገኙት ጸጋ ሙሉ ተስፋ ይኑራችሁ። 14ታዛዦች ልጆች ሆናችሁ ባለማወቅ ቀድሞ የነበራችሁን ክፉ ምኞት አትከተሉ፤ 15ነገር ግን የጠራችሁ እግዚአብሔር ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተም በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ 16“እኔ ቅዱስ ስለ ሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ተብሎ ተጽፎአል። #ዘሌ. 11፥44-45፤ 19፥2።
17ለማንም ሳያዳላ ለያንዳንዱ እንደየሥራው የሚፈርደውን እግዚአብሔርን “አባታችን” ብላችሁ የምትጠሩት ከሆነ በዚህ ዓለም በእንግድነት መጻተኞች ሆናችሁ ስትኖሩ እርሱን በመፍራት ኑሩ። 18እናንተ ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ አኗኗር የተዋጃችሁት ጠፊ በሆነ በብር ወይም በወርቅ አለመሆኑን ታውቃላችሁ። 19እናንተ የተዋጃችሁት ነውር ወይም እንከን እንደሌለው ንጹሕ በግ በሆነው በክርስቶስ ክቡር ደም ነው። 20እርሱ የታወቀው ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ሲሆን፥ አሁን በመጨረሻው ዘመን ስለ እናንተ ተገልጦአል። 21እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ በኢየሱስ አማካይነት እርሱን ከሞት ባስነሣውና ክብርን በሰጠው በእግዚአብሔር ትተማመናላችሁ።
22ለምእመናን ቅንነት የተሞላበት ፍቅር እንዲኖራችሁ ለእውነት በመታዘዝ ነፍሳችሁን አንጽታችኋል፤ ስለዚህ በሙሉ ልባችሁ እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ። #1፥22 በሙሉ፦ አንዳንድ የብራና ጽሑፎች “በንጹሕ” ይላሉ። 23ዳግመኛ የተወለዳችሁት ሕያው በሆነውና ለዘለዓለም ጸንቶ በሚኖረው በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ ከሚጠፋ ዘር አይደለም፤ 24መጽሐፍ እንደሚለው፦
“ሥጋ ለባሽ ሁሉ እንደ ሣር ነው፤
ክብሩም ሁሉ እንደ ዱር አበባ ነው፤
ሣሩም ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤
25የጌታ ቃል ግን
ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል።”
የተሰበከላችሁም የምሥራች ቃል ይኸው ነው። #ኢሳ. 40፥6-8።
Currently Selected:
1 የጴጥሮስ መልእክት 1: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997