YouVersion Logo
Search Icon

1 የጴጥሮስ መልእክት 2

2
ሕያው ድንጋይና ቅዱስ ሕዝብ
1እንግዲህ ክፋትን ሁሉ፥ ማታለልን ሁሉ፥ ግብዝነትን፥ ቅናትን፥ ማንኛውንም ዐይነት ሐሜት አስወግዱ፤ 2አዲስ የተወለዱ ሕፃናት ወተት እንደሚመኙ እናንተም ለመዳን እያደጋችሁ የምትሄዱበትን ንጹሑን መንፈሳዊ ትምህርት ተመኙ። 3ልትመኙ የምትችሉትም “ጌታ ለጋስ መሆኑን ዐውቃችሁ እንደ ሆነ ነው።” #መዝ. 34፥8።
4ስለዚህ ሕያው ድንጋይ ወደ ሆነው ወደ ጌታ ኢየሱስ ቅረቡ፤ ይህ ድንጋይ ሰዎች ንቀው የተዉት፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን የተመረጠና ክቡር ዋጋ ያለው ነው። 5ወደ ጌታ ኢየሱስ የምትቀርቡትም እንደ ሕያዋን ድንጋዮች መንፈሳዊ ቤት ሆናችሁ ለመታነጽ ነው፤ በዚህ ዐይነት በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር ለማቅረብ ቅዱሳን ካህናት ትሆናላችሁ። 6በቅዱስ መጽሐፍ
“እነሆ! የተመረጠና ክቡር የሆነ
የማእዘን ድንጋይ በጽዮን አኖራለሁ፤
በእርሱም የሚያምን አያፍርም”
የሚል ቃል ተጽፎ ይገኛል። #ኢሳ. 28፥16። 7እንግዲህ ለእናንተ ለምታምኑት ይህ ድንጋይ ክቡር ነው፤ ለማያምኑት ግን
“ግንበኞች ንቀው የጣሉት ድንጋይ
የማእዘን ራስ ሆነ።” #መዝ. 118፥22።
8ደግሞም፥
“እነሆ! ሰዎችን የሚያሰናክል ድንጋይ፤
እነሆ! ሰዎችን አደናቅፎ የሚጥል አለት” ይላል።
እነርሱ ቃሉን ባለማመናቸው ይሰናከላሉ፤ አስቀድመውም ለዚህ የተመደቡ ናቸው። #ኢሳ. 8፥14-15።
9እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚያስደንቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን አስደናቂ ሥራ እንድታውጁ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ እግዚአብሔር ለራሱ ያደረጋችኹ ቅዱስ ሕዝብ ናችሁ። #ዘፀ. 19፥5-6፤ ኢሳ. 43፥20-21፤ ዘዳ. 4፥20፤ 7፥6፤ 14፥2፤ ቲቶ 2፥14፤ ኢሳ. 9፥2። 10እናንተ ቀድሞ የእግዚአብሔር ሕዝብ አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ ናችሁ፤ ቀድሞ ምሕረት አላገኛችሁም ነበር፤ አሁን ግን ምሕረት አግኝታችኋል። #ሆሴዕ 2፥23።
የእግዚአብሔር አገልጋዮች
11ወዳጆች ሆይ፥ በዚህ ዓለም እንግዶችና መጻተኞች ስለ ሆናችሁ ከነፍስ ጋር ከሚዋጉት ከሥጋ ፍትወቶች እንድትርቁ ዐደራ እላችኋለሁ። 12ምናልባት “ክፉ አድራጊዎች ናቸው” ብለው ቢያሙአችሁም እንኳ እግዚአብሔር እኛን ለመጐብኘት በሚመጣበት ቀን አሕዛብ መልካም ሥራችሁን አይተው እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑ በእነርሱ መካከል ስትኖሩ መልካም ጠባይ ይኑራችሁ።
13ስለ ጌታ ኢየሱስ ብላችሁ ሥልጣን ለተሰጣቸው ሕዝባዊ ድርጅቶች ታዘዙ፤ የበላይ ባለሥልጣን ስለ ሆነ ለንጉሠ ነገሥቱም ታዘዙ። 14ለአገረ ገዢዎችም ታዘዙ፤ እነርሱ ክፉ አድራጊዎችን ለመቅጣት፥ መልካም አድራጊዎችን ለማመስገን ከንጉሠ ነገሥቱ የሚላኩ ናቸው። 15መልካም በማድረግ የሞኞችን አላዋቂ ንግግር ዝም እንድታሰኙ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። 16እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ሆናችሁ በነጻነት ኑሩ እንጂ ነጻነታችሁን የክፋት መሸፈኛ አታድርጉት። 17ሰውን ሁሉ አክብሩ፤ ወንድሞችን ውደዱ፤ እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ንጉሥን አክብሩ።
የክርስቶስ መከራ ምሳሌነት
18እናንተ አገልጋዮች ለጌቶቻችሁ በአክብሮት ታዘዙ፤ የምትታዘዙትም ለደጎቹና ለገሮቹ ብቻ ሳይሆን ለክፉዎችም ነው። 19ሰው የሚመሰገነው በግፍ መከራ ሲቀበል ስለ እግዚአብሔር ብሎ ቢታገሥ ነው። 20ክፉ አድርጋችሁ ቅጣት ስትቀበሉ ብትታገሡ ምን ምስጋና ይኖራችኋል? ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራ ስትቀበሉ ብትታገሡ ከእግዚአብሔር ምስጋና ታገኛላችሁ። 21የተጠራችሁትም ለዚሁ ነው፤ የእርሱን አርአያነት እንድትከተሉ ክርስቶስ ለእናንተ መከራን በመቀበል ምሳሌ ሆኖላችኋል። 22እርሱ ምንም ኃጢአት አላደረገም፤ በአፉ ተንኰል አልተገኘበትም። #ኢሳ. 53፥9። 23ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፤ መከራን ሲቀበል በጽድቅ ለሚፈርደው አምላክ ራሱን ዐደራ ሰጠ እንጂ አልዛተም። #ኢሳ. 53፥7። 24ከኃጢአት ተለይተን በጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በመስቀል ላይ ተሸከመ፤ በእርሱ ቊስል እናንተ ተፈውሳችኋል። #ኢሳ. 53፥5። 25እናንተ እንደ ጠፉ በጎች ትቅበዘበዙ ነበር፤ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል። #ኢሳ. 53፥6።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in