1 የጴጥሮስ መልእክት 4
4
በቅድስና መኖር
1ክርስቶስ በሥጋው መከራ የተቀበለ ስለ ሆነ እናንተም የጦር መሣሪያን እንደ ታጠቀ ሰው በዚህ ሐሳብ በርትታችሁ ተዘጋጁ፤ በሥጋው መከራን የተቀበለ ሰው ኃጢአት መሥራትን አቋርጧል። 2ከእንግዲህ ወዲህም በቀሪው ምድራዊ ኑሮው የሚኖረው የሥጋን ክፉ ምኞት በማድረግ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመፈጸም ነው። 3አሕዛብ እንደሚያደርጉት በስድነት፥ በፍትወት፥ በስካር፥ ቅጥ ባጣ ፈንጠዝያ፥ ያለ ልክ ጠጥቶ በመጨፈርና አጸያፊ በሆነ የጣዖት አምልኮ ያሳለፋችሁት ዘመን ይበቃል። 4አሁን ግን በዚህ ነገር አለመጠን ከእነርሱ ጋር በመቅበጥ ባለመሳተፋችሁ ይደነቃሉ፤ ይሰድቡአችኋልም። 5ነገር ግን በሕይወት ባሉትና በሞቱት ላይ ሊፈርድ ለተዘጋጀው ለእርሱ መልስ ይሰጡበታል። 6ለሙታን ሳይቀር ወንጌል የተሰበከውም በዚህ ምክንያት ነው፤ በዚህ ዐይነት በሥጋቸው እንደ ሰው ሁሉ ይፈረድባቸዋል፤ በመንፈሳቸው ግን እግዚአብሔር በሚኖረው ዐይነት በሕይወት ይኖራሉ።
የእግዚአብሔር ስጦታዎችን በመልካም ማስተዳደር
7እንግዲህ የሁሉ ነገር መጨረሻ ቀርቦአል፤ በትጋት መጸለይ እንድትችሉ የረጋ አእምሮ ይኑራችሁ፤ በመጠንም ኑሩ። 8ፍቅር ብዙ ኃጢአትን ስለሚሸፍን ከሁሉ በላይ እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ። #ምሳ. 10፥12። 9ያለ ማጒረምረም እርስ በርሳችሁ በእንግድነት ተቀባበሉ። 10የተለያዩትን የእግዚአብሔርን የጸጋ ስጦታዎች በታማኝነት በማስተዳደር ከእናንተ እያንዳንዱ በተሰጠው የጸጋ ስጦታ ሌላውን ያገልግል። 11የሚያስተምር፥ የእግዚአብሔርን ቃል እንደሚያስተምር ያስተምር፤ የሚያገለግልም እግዚአብሔር በሚሰጠው ኀይል ያገልግል፤ በዚህም ዐይነት እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሁሉ ነገር ይመሰገናል፤ ክብርና ሥልጣን ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ለእርሱ ይሁን፤ አሜን።
በመከራ ጊዜ መጽናት
12ወዳጆች ሆይ! እንደ እሳት በሚፈትን መከራ ውስጥ ስትገኙ ያልተለመደ እንግዳ ነገር እንደ ደረሰባችሁ አድርጋችሁ አትደነቁ፤ 13ይልቅስ የክርስቶስ ክብር በሚገለጥበት ጊዜ እጅግ ደስ እንዲላችሁ የእርሱ መከራ ተካፋዮች በሆናችሁበት መጠን ደስ ይበላችሁ። 14ስለ ክርስቶስ ስም ብትሰደቡ የክብር መንፈስ ማለት የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ስለሚያርፍ ደስ ይበላችሁ። 15ከእናንተ ማንም መከራ ሲቀበል እንደ ነፍሰ ገዳይ፥ እንደ ሌባ፥ እንደ ወንጀለኛ፥ በሰው ጉዳይ ጣልቃ እንደሚገባ አይሁን። 16ክርስቲያን በመሆኑ መከራ የሚደርስበት ቢኖር ግን ስለ ክርስቶስ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር።
17ፍርድ የሚጀመርበት ጊዜ ቀርቦአል፤ ፍርዱ የሚጀመረውም በእግዚአብሔር ሰዎች ላይ ነው፤ ታዲያ፥ ፍርድ የሚጀመረው በእኛ ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ ሰዎች መጨረሻቸው ምን ይሆን? 18ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚለው፦
“ጻድቅ እንኳ መዳን የሚችለው በጭንቅ ከሆነ
እግዚአብሔርን የማያመልኩ ሰዎች እንዴት ሊሆኑ ነው?” #ምሳ. 11፥31።
19ስለዚህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራ የሚቀበሉ ሰዎች ሁለንተናቸውን ለታማኙ ፈጣሪ ዐደራ ሰጥተው መልካም ነገርን ከማድረግ አይቈጠቡ።
Currently Selected:
1 የጴጥሮስ መልእክት 4: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997