1 ወደ ጢሞቴዎስ 4
4
ሐሰተኞች መምህራን
1መንፈስ ቅዱስ ግን በግልጥ እንዲህ ይላል፤ “በኋለኛው ዘመን አንዳንድ ሰዎች አሳሳች መናፍስትንና የአጋንንትን ትምህርት በመከተል ሃይማኖትን ይክዳሉ።” 2እንዲህም ዐይነቱ ትምህርት የሚመነጨው በግብዝነት፥ ሐሰትን ሲናገሩ በጋለ ብረት እንደ ተተኮሰ ያኽል ሆኖ የደነዘዘ ኅሊናቸው ከማይወቅሳቸው ሰዎች ነው። 3እንደእነዚህ ያሉት ሰዎች ጋብቻን ይከለክላሉ፤ የሚያምኑና እውነትን የሚያውቁ ሰዎችም እርሱን እያመሰገኑ እንዲመገቡት እግዚአብሔር የፈጠረላቸውን ምግብ “አትብሉ” እያሉ ይከለክላሉ። 4ዳሩ ግን እግዚአብሔር የፈጠረው ነገር ሁሉ መልካም ነው፤ በምስጋና ከተቀበሉት ምንም የሚጣል ነገር የለም። 5በእግዚአብሔር ቃልና በጸሎት የተቀደሰ ይሆናል።
የክርስቶስ መልካም አገልጋይ ስለ መሆን
6ይህን ትምህርት ለአማኞች ብታስገነዝብ የእምነትን ቃልና የምትከተለውን መልካም ትምህርት እየተመገብክ ያደግኽ፥ የኢየሱስ ክርስቶስ መልካም አገልጋይ ትሆናለህ። 7እግዚአብሔርን ማምለክ ከሌለበት ከዓለማዊ አፈ ታሪክ ራቅ፤ እግዚአብሔርንም ማምለክ ራስህን አለማምድ። 8በሰውነት ማጠንከሪያ ትምህርት ራስን ማለማመድ ጥቅሙ ጥቂት ነው፤ እግዚአብሔርን ማምለክ ማለማመድ ግን ለአሁንና ለሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው ለሁሉ ነገር ይጠቅማል። 9ይህም አባባል ሰው ሁሉ ሊቀበለው የሚገባ እውነተኛ ነገር ነው። 10እኛ ሰዎችን ሁሉ ይልቁንም የሚያምኑትን ሁሉ በሚያድን በሕያው አምላክ ተስፋ የምናደርግ ስለ ሆነ በሥራ እንደክማለን፤ እንታገላለን። #4፥10 እንታገላለን፦ አንዳንድ ቅጂዎች እንሰደባለን ይላሉ።
11እነዚህን ነገሮች እዘዝ፤ አስተምርም፤ 12ወጣት በመሆንህ ማንም አይናቅህ፤ ይልቅስ በንግግር፥ በኑሮ፥ በፍቅር፥ በእምነትና በንጽሕና ለአማኞች መልካም ምሳሌ ሁን። 13እኔ እስክመጣ ድረስ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለሕዝብ በማንበብ፥ በመስበክና በማስተማር ትጋ። 14ትንቢት በተነገረልህ ጊዜና የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችም እጃቸውን በጫኑብህ ጊዜ የተሰጠህን በአንተ ያለውን መንፈሳዊ ስጦታ አትዘንጋ። 15መሻሻልህን ሰዎች ሁሉ እንዲያዩ በእነዚህ ነገሮች ትጋ፤ እነዚህንም ነገሮች በሥራ ላይ በማዋል ሁለንተናህን ለእነርሱ ስጥ። 16ለራስህና ለማስተማር ሥራህ ተጠንቀቅ፤ በእነዚህም ነገሮች ጽና፤ ይህን በማድረግም ራስህንና የሚሰሙህን ታድናለህ።
Currently Selected:
1 ወደ ጢሞቴዎስ 4: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997