2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4
4
እውነተኛ ሐዋርያዊ አገልግሎት
1እግዚአብሔር በምሕረቱ ይህን አገልግሎት ስለ ሰጠን ተስፋ አንቈርጥም። 2ስውርና አሳፋሪ የሆነውን ነገር አስወግደናል፤ በተንኰልም አንሠራም፤ የእግዚአብሔርንም ቃል አንለውጥም፤ ይልቅስ እውነትን በይፋ እናሳያለን፤ ራሳችንንም ለሰው ሁሉ ኅሊና በእግዚአብሔር ፊት ግልጥ እናደርጋለን። 3ያስተማርነው የወንጌል ቃል ምናልባት የተሰወረ ቢሆንም የተሰወረው ለሚጠፉት ነው። 4የዚህ ዓለም ገዢ የሆነው ሰይጣን የማያምኑትን ሰዎች ልብ አሳወረው፤ በዚህም በእግዚአብሔር መልክ የተገለጠው የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል የሚያበራላቸውን ብርሃን እንዳያዩ አደረጋቸው። 5እኛ የምናስተምረው ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ መሆኑንና እኛም ራሳችን ስለ ኢየሱስ የእናንተ አገልጋዮች መሆናችንን ነው እንጂ ስለ ራሳችንስ አንሰብክም። 6“ብርሃን በጨለማ ውስጥ ይብራ!” ብሎ የተናገረ እግዚአብሔር በክርስቶስ መልክ የሚያበራውን የእግዚአብሔርን ክብር የማወቅ ብርሃን እንዲሰጠን ብርሃኑን በልባችን ውስጥ እንዲበራ አደረገ። #ዘፍ. 1፥3።
7ነገር ግን ይህ ከሁሉ የሚበልጠው ኀይል የእግዚአብሔር እንጂ የእኛ አለመሆኑ እንዲታወቅ ይህን ክቡር ነገር እንደ ሸክላ ዕቃ ሆነን ይዘነዋል። 8በየአቅጣጫው መከራ ይደርስብናል፤ ግን አንሸነፍም፤ ብዙ ጊዜ ግራ ይገባናል፤ ግን ተስፋ አንቈርጥም፤ 9ጠላቶች ያሳድዱናል፤ ግን ወዳጆች አጥተን አናውቅም፤ ተመተን እንወድቃለን፤ ግን አንሞትም፤ 10የኢየሱስ ሕይወት በእኛ ሰውነት እንዲገለጥ በኢየሱስ ላይ የደረሰው ሞት በእኛም ሰውነት ላይ ዘወትር ተሸክመን እንዞራለን። 11የኢየሱስ ሕይወት በሟች ሰውነታችን ይገለጥ ዘንድ እኛ ሕያዋኑ ስለ ኢየሱስ ሁልጊዜ ለሞት ተላልፈን እንሰጣለን። 12ስለዚህ እኛ መላልሰን ለሞት ስንጋለጥ እናንተ ግን ለሕይወት ትጋለጣላችሁ።
13ይሁን እንጂ “አመንኩ፤ ስለዚህ ተናገርኩ” ተብሎ እንደ ተጻፈው፥ እኛም ያው አንዱ የእምነት መንፈስ ስላለን እናምናለን፤ ስለዚህም እንናገራለን። #መዝ. 116፥10። 14ጌታ ኢየሱስን ከሞት ያስነሣ አምላክ እኛንም ከኢየሱስ ጋር እንደሚያስነሣንና ከእናንተም ጋር በፊቱ እንደሚያቀርበን እናውቃለን። 15ይህ ሁሉ ለእናንተ ጥቅም የሆነው ጸጋ ተትረፍርፎ ለብዙ ሰዎች በደረሰ መጠን ለእግዚአብሔር ክብር የሚሆነው ምስጋና እንዲበዛ ነው።
በእምነት መኖር
16ስለዚህ ተስፋ አንቈርጥም፤ ምንም እንኳ የውጪው ሰውነታችን ቢጠፋ የውስጡ ሰውነታችን በየቀኑ ይታደሳል። 17ይህም ቀላልና ጊዜያዊ የሆነ መከራችን ወደር የሌለውን እጅግ ታላቅ የሆነ ዘለዓለማዊ ክብር ያስገኝልናል። 18እኛ የምንጠብቀው የማይታየውን ነገር እንጂ የሚታየውን አይደለም፤ የሚታየው ነገር ጊዜያዊ ነው፤ የማይታየው ግን ዘለዓለማዊ ነው።
Currently Selected:
2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997