YouVersion Logo
Search Icon

2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7

7
1እንግዲህ ወዳጆቼ ሆይ፥ ይህ ሁሉ ተስፋ የተሰጠው ለእኛ ስለ ሆነ ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ከማናቸውም ነገር ራሳችንን እናንጻ፤ እግዚአብሔርንም በመፍራት ቅድስናችን ፍጹም እንዲሆን እናድርግ።
የጳውሎስ ደስታ
2ከልባችሁ ተቀበሉን፤ እኛ ማንንም አልበደልንም፤ ማንንም አልጐዳንም፤ ማንንም መጠቀሚያ አላደረግንም። 3ይህንንም የምለው በእናንተ ላይ ለመፍረድ አይደለም። ከዚህ በፊት እንደ ነገርኳችሁ እናንተ በልባችን ውስጥ ናችሁ፤ ስለዚህ በሕይወትም ሆነ በሞት ሁልጊዜ ከእናንተ አንለይም። 4በእናንተ ላይ ያለኝ እምነት ከፍተኛ ነው፤ በእናንተ ላይ ያለኝ ትምክሕት ትልቅ ነው፤ በእናንተም እጽናናለሁ፤ በመከራችን ሁሉ በጣም እደሰታለሁ።
5መቄዶንያ በደረስን ጊዜ እንኳ ከብዙ አቅጣጫ ችግር ደረሰብን እንጂ ምንም ዕረፍት አላገኘንም፤ በውጭ ጠብ በውስጥም ፍርሀት ነበረብን። #2ቆሮ. 2፥13። 6ነገር ግን የተዋረዱትን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን። 7የተጽናናነውም በእርሱ መምጣት ብቻ ሳይሆን እናንተ እርሱን ያጽናናችሁት መሆኑን በመስማታችንም ጭምር ነው፤ ስለ እኔ ያላችሁን ናፍቆትና ሐዘን ጭንቀትም በነገረን ጊዜ ይበልጥ ደስ አለኝ።
8ከዚህ በፊት የጻፍኩላችሁ መልእክት ያሳዘናችሁ ቢሆንም እንኳ መልእክቱን በመጻፌ አልጸጸትም፤ ተጸጽቼም ብሆን እንኳ የተጸጸትኩት መልእክቴ ለጥቂት ጊዜ ስላሳዘናችሁ ነው። 9አሁን ግን ደስ ብሎኛል፤ የተደሰትኩበትም ምክንያት እናንተን ስላሳዘንኳችሁ ሳይሆን በሐዘናችሁ ምክንያት ንስሓ ገብታችሁ በመለወጣችሁ ነው፤ እንግዲህ ሐዘናችሁ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ሆነ እኛ ምንም አልበደልናችሁም ማለት ነው። 10እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚሆን ሐዘን ወደ መዳን የሚመራ በንስሓ የሚገኘውን ለውጥ ስለሚያስገኝ ጸጸትን አያስከትልም፤ ዓለማዊ ሐዘን ግን ሞትን ያመጣል። 11ይህ ሐዘናችሁ በእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑ እንዴት ያለ የመከላከያ መልስ መስጠትን፥ እንዴት ያለ ቶሎ መቈጣትን፥ እንዴት ያለ ፍርሀትን፥ እንዴት ያለ ናፍቆትን፥ እንዴት ያለ ቅናትን፥ እንዴት ያለ ቅጣትንም እንዳስከተለ ልብ ብላችሁ አስተውሉ። እናንተ ደግሞ በሁሉም ነገር ከጉዳዩ ነጻ መሆናችሁን አስመስክራችኋል።
12ስለዚህ ምንም እንኳ ለእናንተ ብጽፍ እኔ የጻፍኩላችሁ ስለ እኛ ያላችሁ ትጋት በእግዚአብሔር ፊት ለእናንተ ግልጥ እንዲሆን ብዬ ነው እንጂ በደል ስለ ሠራውና በደል ስለ ተፈጸመበት ሰው ብዬ አይደለም። 13ከመጽናናታችንም በላይ ቲቶ ባገኘው ደስታ ይበልጥ ተደስተናል፤ የተደሰትነውም ሁላችሁም ቲቶን ስላጽናናችሁትና መንፈሱንም ስላሳረፋችሁት ነው። 14በእናንተ የነበረኝን ትምክሕት ለቲቶ ነግሬው ነበር፤ እናንተም አላሳፈራችሁኝም፤ ሁልጊዜ እውነትን እንነግራችሁ ነበር፤ ይህም ስለ እናንተ ለቲቶ የነገርነው ትምክሕት እውነት በመሆኑ ተረጋግጦአል። 15ሁላችሁም ታዛዦች እንደ ሆናችሁና በፍርሃትና በመንቀጥቀጥም እንደ ተቀበላችሁት ቲቶ ሲያስታውስ፥ ለእናንተ ያለው ፍቅር በጣም ታላቅ ሆኖአል። 16እኔም በሁሉ መንገድ በእናንተ ለመተማመን በመቻሌ ይበልጥ ደስ ብሎኛል።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in