2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6
6
1ከእግዚአብሔር ጋር አብረን የምንሠራ እንደ መሆናችን የተቀበላችሁትን ጸጋ በከንቱ አታስቀሩት ብለን እንለምናችኋለን። 2እግዚአብሔር፦
“ተስማሚ በሆነ ጊዜ ሰማሁህ!
በመዳን ቀን ረዳሁህ!” ስለሚል፥
“እነሆ ተስማሚ የሆነው ጊዜ አሁን ነው፤ የመዳኛው ቀን አሁን ነው።” #ኢሳ. 49፥8።
3አገልግሎታችን እንዳይነቀፍ በምንም ነገር ለማንም መሰናከያ አንሆንም። 4ይልቅስ መከራንና ችግርን ጭንቀትንም እየታገሥን እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን በማናቸውም መንገድ እናቀርባለን። 5የእግዚአብሔር አገልጋዮች መሆናችንን የምንገልጠውም በመገረፍ፥ በመታሰር፥ በመታወክ፥ በሥራ በመድከም፥ እንቅልፍ በማጣትና በመራብ ነው፤ #ሐ.ሥ. 16፥23። 6እንዲሁም በንጽሕና፥ በዕውቀት፥ በትዕግሥት፥ በደግነት፥ በመንፈስ ቅዱስ በመመራትና ግብዝነት በሌለበት ፍቅር፥ 7በእውነት ቃልና በእግዚአብሔር ኀይል ነው። የማጥቂያም ሆነ የመከላከያ መሣሪያችን ጽድቅ ነው፤ 8ለክብር ወይም ለውርደት ለመወቀስ ወይም ለመመስገን የተዘጋጀን ነን፤ እውነተኞች ስንሆን፥ አታላዮች ተባልን። 9የታወቅን ስንሆን፥ እንዳልታወቅን ሆነን፥ ሞተዋል ስንባል፥ ሕያዋን ሆነን እንገኛለን፤ ብንደበደብም አልተገደልንም፤ 10ሐዘን ቢደርስብንም ዘወትር እንደሰታለን፤ ድኾች ሆነን ሳለ፥ ብዙዎችን ሀብታሞች እናደርጋለን፤ ምንም የሌለን ስንሆን፥ ሁሉ ነገር አለን።
11እናንተ በቆሮንቶስ የምትኖሩ ሰዎች ሆይ! እነሆ፥ በግልጥ ተናግረናችኋል፤ ልባችንንም በሰፊው ከፍተንላችኋል። 12እናንተ ፍቅራችሁን ነፈጋችሁን እንጂ እኛስ አልነፈግናችሁም። 13አባት ለልጆቹ እንደሚናገር ልናገርና፥ እኛ ልባችንን በሰፊው ከፍተን ስሜታችንን እንደ ገለጥንላችሁ እናንተም እንዲሁ አድርጉ።
ከማያምኑ ሰዎች ጋር አለመተባበር
14በማይመች ሁኔታ ከማያምኑ ሰዎች ጋር አትጣመሩ፤ ጽድቅና ኃጢአት እንዴት ሊተባበሩ ይችላሉ? ብርሃንና ጨለማ እንዴት አብረው ሊኖሩ ይችላሉ? 15ክርስቶስና ዲያብሎስ እንዴት ሊስማሙ ይችላሉ? የሚያምንና የማያምንስ በምን ሊወዳጁ ይችላሉ? #6፥15 ዲያብሎስ፦ በግሪክ “ቤልያል” ወይም “ቤልያር” በዕብራይስጥ “ቤሊዐል” ተብሎ ይጠቀሳል። ትርጒሙ “ዋጋ ቢስ” ወይም “ሕግ የለሽ” ማለት ሲሆን ለሰይጣን መጠሪያ ሆኖ ገብቶአል። 16የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከጣዖቶች ጋር ምን ስምምነት አለው? እግዚአብሔርም፦
“መኖሪያዬን በሕዝቤ መካከል አደርጋለሁ፤
ከእነርሱም ጋር እኖራለሁ፤
እኔ አምላካቸው እሆናለሁ፤
እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ”
ብሎ እንደ ተናገረው እኛ እያንዳንዳችን የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነን። #ዘሌ. 26፥12፤ ሕዝ. 37፥27፤ 1ቆሮ. 3፥16፤ 6፥19። 17ደግሞም ጌታ እንዲህ ብሎአል፦
“ከእነርሱ መካከል ተለይታችሁ ውጡ፤
ርኩስ የሆነውንም ነገር አትንኩ፤
እኔም እቀበላችኋለሁ፤ #ኢሳ. 52፥11።
18እኔ አባታችሁ እሆናለሁ፤
እናንተም ወንዶችና ሴቶች ልጆቼ ትሆናላችሁ፥
ይላል ሁሉን ቻይ አምላክ።” #2ሳሙ. 7፥14፤ 1ዜ.መ. 17፥13፤ ኢሳ. 43፥6፤ ኤር. 31፥9።
Currently Selected:
2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997