የሐዋርያት ሥራ 1
1
1ቴዎፍሎስ ሆይ! #ሉቃ. 1፥1-4።
በመጀመሪያ መጽሐፌ ኢየሱስ የሠራውንና ያስተማረውን ሁሉ ጽፌአለሁ። የጻፍኩትም ኢየሱስ ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ 2ወደ ሰማይ እስከ ዐረገበት ቀን ድረስ የሠራውን ነው፤ ወደ ሰማይ ያረገውም ለመረጣቸው ሐዋርያት ትእዛዙን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ከሰጣቸው በኋላ ነው፤ 3ብዙ መከራ ተቀብሎ ከሞተ በኋላ በብዙ ግልጥ ማስረጃዎች ሕያው ሆኖ ታያቸው፤ አርባ ቀን ሙሉ እየተገለጠላቸውም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት አስተማራቸው። 4አብሮአቸውም በነበረ ጊዜ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “እኔ የነገርኳችሁን ከአብ የተሰጠ ተስፋ ጠብቁ እንጂ ከኢየሩሳሌም አትውጡ፤ #ሉቃ. 24፥29። 5ዮሐንስ በውሃ አጠመቀ፤ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ።” #ማቴ. 3፥11፤ ማር. 1፥8፤ ሉቃ. 3፥16፤ ዮሐ. 1፥33።
ኢየሱስ ወደ ሰማይ ማረጉ
(ማር. 16፥19-20፤ ሉቃ. 24፥50-53)
6እነርሱ በአንድነት ተሰብስበው ሳሉ፥ “ጌታ ሆይ! መንግሥትን ለእስራኤል መልሰህ የምትሰጥበት ጊዜ አሁን ነውን?” ሲሉ ጠየቁት።
7ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “አብ በገዛ ሥልጣኑ የወሰነውን ጊዜና ዘመን እናንተ ልታውቁት አትችሉም። 8ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኀይልን ትቀበላላችሁ፤ በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም፥ በይሁዳ ምድር ሁሉ፥ በሰማርያ፥ እስከ ምድርም ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ።” #ማቴ. 28፥19፤ ማር. 16፥15፤ ሉቃ. 24፥47-48። 9ይህንንም ካለ በኋላ እነርሱ እያዩት ወደ ሰማይ ዐረገ፤ ደመናም ተቀብሎ ከዐይናቸው ሰወረው። #ማር. 16፥19፤ ሉቃ. 24፥50-51።
10እርሱ እያረገ ሳለ፥ እነርሱ ትኲር ብለው ወደ ሰማይ ሲመለከቱ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች አጠገባቸው ቆመው፥ 11“እናንተ የገሊላ ሰዎች፥ ስለምን ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ቆማችኋል? ይህ ወደ ሰማይ ሲያርግ ያያችሁት ኢየሱስ፥ ወደ ሰማይ ሲያርግ ባያችሁት ዐይነት ተመልሶ ይመጣል” አሉአቸው።
በይሁዳ ምትክ ማትያስ መመረጡ
(መዝ. 109፥8)
12ከዚህ በኋላ ደብረ ዘይት ከተባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ የደብረ ዘይት ተራራ ከኢየሩሳሌም የሚርቀው የሰንበት መንገድ (አንድ ኪሎ ሜትር) ያኽል ነው። 13ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ወደሚኖሩበት ሰገነት ላይ ወጡ፤ እነርሱም “ጴጥሮስ፥ ዮሐንስ፥ ያዕቆብ፥ እንድርያስ፥ ፊልጶስ፥ ቶማስ፥ በርተሎሜዎስ፥ ማቴዎስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፥ ቀናተኛው ስምዖንና የያዕቆብ ልጅ ይሁዳ” ናቸው። #1፥13 ቀናተኛው፦ የማር. ም. 3 ቊ. 18 ገለጻን ተመልከቱ። #ማቴ. 10፥2-4፤ ማር. 3፥16-19፤ ሉቃ. 6፥14-16። 14እነዚህ ሁሉ ዘወትር ለጸሎት በአንድነት ይሰበሰቡ ነበር፤ ከእነርሱም ጋር አንዳንድ ሴቶችና የኢየሱስ እናት ማርያም፥ እንዲሁም የኢየሱስ ወንድሞች ነበሩ።
15በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መቶ ኻያ በሚያኽሉ አማኞች መካከል ቆመና እንዲህ አለ፦ 16“ወንድሞች ሆይ፥ ኢየሱስን ለያዙት ሰዎች መሪ ስለ ሆናቸው ስለ ይሁዳ፥ መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በዳዊት አፍ የተናገረው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል መፈጸም ነበረበት። 17ይሁዳ ከእኛ አንዱ ሆኖ የዚህ አገልግሎታችን ተካፋይ ነበር። 18ነገር ግን ይህ ሰው በክፉ ሥራው ዋጋ መሬት ገዛ፤ በግንባሩም ተደፍቶ ከመካከሉ ተሰነጠቀ፤ አንጀቱም ተዘረገፈ፤ #ማቴ. 27፥3-8። 19ይህም ነገር በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሁሉ ታወቀ፤ ስለዚህ ያ መሬት በቋንቋቸው ‘አኬልዳማ’ ተብሎ ተጠራ፤ ትርጓሜውም ‘የደም መሬት’ ማለት ነው።
20“ይህም የሆነበት ምክንያት በመዝሙር መጽሐፍ፥
‘መኖሪያው ባዶ ይሁን፤
ማንም አይኑርበት፤
ደግሞም ሹመቱን ሌላ ሰው ይውሰድበት’ #መዝ. 69፥25፤ 109፥8።
የሚል ተጽፎ ስለ ነበር ነው።
21“ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ በእኛ መካከል በተመላለሰበት ጊዜ ሁሉ ከእኛ ጋር አብረውን ከነበሩት፥ 22እንዲሁም ከዮሐንስ ጥምቀት ጀምሮ ጌታ ኢየሱስ ወደ ሰማይ እስከ ዐረገበት ቀን ድረስ አብረውን ከነበሩት ከነዚህ ሰዎች አንዱ ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምስክር እንዲሆን ያስፈልጋል።” #ማቴ. 3፥16፤ ማር. 1፥9፤ 16፥19፤ ሉቃ. 3፥21፤ 24፥51።
23ከዚህ በኋላ ሁለት ሰዎች አቀረቡ፤ እነርሱም በርሳባስ ወይም ኢዮስጦስ የሚባለው ዮሴፍና ማትያስ ነበሩ። 24እንዲህ ሲሉም ጸለዩ፦ “የሰውን ሁሉ ልብ የምታውቅ ጌታ ሆይ፥ ከነዚህ ከሁለቱ ማንን እንደ መረጥክ አሳየን፤ 25የምንጸልየውም ይሁዳ ወደ ራሱ ስፍራ ሲሄድ የተወውን አገልግሎትና ሐዋርያነት በመቀበል የሚተካውን እንድትገልጥልን ነው።” 26ዕጣም በጣሉ ጊዜ ዕጣው ለማትያስ ወጣ፤ ስለዚህ እርሱ ከዐሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ተቈጠረ።
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 1: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997