የሐዋርያት ሥራ መግቢያ
መግቢያ
የሐዋርያት ሥራ ከሉቃስ ወንጌል የቀጠለ ነው፤ የመጽሐፉ ዋና ዓላማ የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ተከታዮች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ስለ እርሱ የሚናገረውን የምሥራች ቃል “በኢየሩሳሌም፥ በይሁዳ ምድር ሁሉ፥ በሰማርያ፥ እስከ ምድርም ዳርቻ” (1፥8) ወንጌልን እንዴት እንዳሠራጩ ለመተረክ ነው፤ መጽሐፉ የክርስትና እምነት በአይሁድ መካከል ተጀምሮ የመላው ዓለም ሕዝብ እምነት እስኪሆን ድረስ እንዴት እንደ ተስፋፋ የሚናገር ታሪክ ነው። ጸሐፊው፥ ክርስቲያኖች የሮምን ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ለመቀናቀን ውስጥ ለውስጥ ሤራ የሚፈጽሙ ሰዎች እንዳልሆኑና የክርስትና ሃይማኖት የአይሁድን ሃይማኖት ፍጹም የሚያደርግ እንደ ሆነ ለማስረዳት ብርቱ ጥረት አድርጎአል።
የሐዋርያት ሥራ፥ ስለ ኢየሱስ የሚናገረው የምሥራች ቃል የሚደርስበት ቦታ በየጊዜው እየሰፋ መሄዱንና የቤተ ክርስቲያንን መመሥረት በሚያንጸባርቁ ሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ሊመደብ ይችላል፦
1. የክርስትና ሃይማኖት ከኢየሱስ ዕርገት በኋላ በኢየሩሳሌም ስለ መጀመሩ።
2. በእስራኤል አገር በሙሉ ስለ መዳረሱ።
3. ሮምን ጨምሮ በሜዲቴራኒያን ባሕር ዙሪያ ባሉት አገሮች መስፋፋቱ።
በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ጐላ ብሎ የሚታየው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ሲሆን በጰንጠቆስጤ ቀን በኢየሩሳሌም በነበሩት አማኞች ላይ በኀይል መውረዱን፥ እንዲሁም በመጽሐፉ ውስጥ በተዘረዘሩት ድርጊቶች ሁሉ እንደ ታየው መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንንና መሪዎችዋን መምራቱንና ማበረታታቱን ይጨምራል። በጥንት ጊዜ ይቀርብ የነበረው የክርስትና መልእክት በልዩ ልዩ ስብከቶች ውስጥ፥ በአስተዋጽዖ መልክ ቀርቦአል፤ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የተፈጸሙት ድርጊቶችም መልእክቱ በአማኞች ሕይወትና በቤተ ክርስቲያን ኅብረት የነበረው ኀይል ምን ያኽል ታላቅ መሆኑን ያስረዳሉ።
አጠቃላይ የመጽሐፉ ይዘት
የምስክርነቱ ዝግጅት 1፥1-26
ኢየሱስ በመጨረሻ የሰጠው ትእዛዝና ተስፋ 1፥1-14
በይሁዳ ቦታ የተተካ 1፥15-26
ምስክርነት በኢየሩሳሌም 2፥1—8፥3
ምስክርነት በይሁዳና በሰማርያ 8፥4—12፥25
የጳውሎስ ሐዋርያዊ አገልግሎት 13፥1—28፥31
የመጀመሪያው ሐዋርያዊ ጒዞ 13፥1—14፥28
የኢየሩሳሌም ጉባኤ 15፥1-35
ሁለተኛው ሐዋርያዊ ጒዞ 15፥36—18፥22
ሦስተኛው ሐዋርያዊ ጒዞ 18፥23—21፥16
የጳውሎስ በኢየሩሳሌም፥ በቂሳርያና በሮም መታሰር 21፥17—28፥31
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ መግቢያ: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997