YouVersion Logo
Search Icon

የሐዋርያት ሥራ 5

5
ሐናንያና ሰጲራ
1ሐናንያ የሚባል አንድ ሰው ሰጲራ ከምትባለው ሚስቱ ጋር ሆኖ መሬት ሸጠ፤ 2ሚስቱም እያወቀች ከመሬቱ ሽያጭ ከፊሉን አስቀረና ከፊሉን አምጥቶ ለሐዋርያት አስረከበ፤ 3ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው፦ “ሐናንያ ሆይ! በመንፈስ ቅዱስ ላይ እንድትዋሽና ከመሬቱም ሽያጭ ከፊሉን እንድታስቀር ያደረገህ ሰይጣን ስለምን ወደ ልብህ ገባ? 4ሳትሸጠው በፊት መሬቱ የአንተ አልነበረምን? ከሸጥከውስ በኋላ ገንዘቡ የአንተው አልነበረምን? ታዲያ፥ ይህን ነገር ስለምን በልብህ አሰብክ? የዋሸኸው በእግዚአብሔር ላይ ነው እንጂ በሰው ላይ አይደለም።” 5ሐናንያ ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ወደቀና ሞተ፤ ይህን ነገር የሰሙ ሰዎች ሁሉ እጅግ ፈሩ። 6ጐልማሶች ተነሥተው አስከሬኑን ከፈኑና ወስደው ቀበሩት።
7ከሦስት ሰዓት ያኽል በኋላ የሐናንያ ሚስት በባልዋ ላይ የደረሰውን ሁናቴ ሳታውቅ መጣች። 8ጴጥሮስም “እስቲ ንገሪኝ መሬታችሁን የሸጣችሁት ይህን ለሚያኽል ገንዘብ ነውን?” አላት። እርስዋም “አዎ! ይህን ለሚያኽል ገንዘብ ነው” አለች።
9በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “የእግዚአብሔርን መንፈስ ለመፈታተን እንዴት ተስማማችሁ? እነሆ! ባልሽን ቀብረው የሚመለሱት ሰዎች በበር ናቸው፤ አንቺንም ወስደው ይቀብሩሻል” አላት። 10እርስዋም በድንገት በእግሩ ሥር ወደቀችና ሞተች፤ ጐልማሶችም ሲገቡ ሞታ አገኙአትና ወስደው በባልዋ አጠገብ ቀበሩአት። 11በቤተ ክርስቲያን ሁሉና ይህን ነገር በሰሙ ሰዎች ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሀት ሆነ።
በሐዋርያት እጅ የተደረጉ ተአምራትና ድንቅ ነገሮች
12ብዙ ተአምራትና ድንቅ ነገሮች በሕዝቡ መካከል በሐዋርያት እጅ ይደረጉ ነበር፤ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው በሰሎሞን መመላለሻ ይሰበሰቡ ነበር። 13ከእነርሱ ውጪ ከሆኑት ሰዎች አንድ እንኳ ከእነርሱ ጋር ለመሆን የሚደፍር አልነበረም፤ ይሁን እንጂ ሕዝቡ ያከብራቸው ነበር። 14በጌታ የሚያምኑ ወንዶችና ሴቶች ቊጥራቸው በጣም እየበዛ ይሄድ ነበር። 15ሰዎች ብዙ በሽተኞችን ወደ መንገድ እያወጡ በአልጋ ላይና በቃሬዛ ላይ ያስተኙአቸው ነበር፤ እንዲህም ያደረጉት ጴጥሮስ በዚያ በኩል ሲያልፍ ጥላው እንኳ በአንዳንዶቹ ላይ እንዲያርፍባቸው ነበር። 16ሰዎች በኢየሩሳሌም ዙሪያ ካሉት ከተሞች በሽተኞቻቸውንና በርኩሳን መናፍስት የሚሠቃዩትን ያመጡ ነበር፤ ሁሉም ይድኑ ነበር።
በሐዋርያት ላይ ስደት መነሣቱ
17የካህናት አለቃውና ከእርሱ ጋር የነበሩት የሰዱቃውያን ወገኖች ሁሉ በቅንነት ተሞልተው በእነርሱ ላይ ተነሡ፤ 18ሐዋርያትን ያዙና በሕዝቡ ወህኒ ቤት አስገቡአቸው። 19የእግዚአብሔር መልአክ ግን በሌሊት የወህኒ ቤቱን በሮች ከፍቶ፥ አስወጣቸውና፥ 20“ሂዱ! በቤተ መቅደስ ቆማችሁ የዚህን ሕይወት ቃል ሁሉ ለሕዝቡ ንገሩ!” አላቸው፤ 21ሐዋርያቱም ትእዛዙን ተቀብለው በማለዳ ወደ ቤተ መቅደስ ገቡና ማስተማር ጀመሩ። በዚያን ጊዜ የካህናት አለቃውና ከእርሱ ጋር የነበሩት መጥተው የሸንጎውን አባሎችና የአይሁድ ሽማግሌዎችን ሁሉ በአንድነት ሰበሰቡ፤ ሐዋርያትንም እንዲያመጡአቸው ሰዎችን ወደ ወህኒ ቤት ላኩ። 22የዘብ ኀላፊዎቹ ግን ወደ ወህኒ ቤት ሄደው ሐዋርያትን በዚያ አላገኙአቸውም፤ ተመልሰውም መጡና 23“የወህኒ ቤቱ በር በጥብቅ ተቈልፎ ጠባቂዎችም በበሩ ፊት ቆመው አገኘናቸው፤ የወህኒ ቤቱን በር በከፈትነው ጊዜ ግን በውስጥ ማንንም አላገኘንም” ብለው ተናገሩ። 24የቤተ መቅደሱ የዘብ አዛዥና የካህናት አለቆች ይህን በሰሙ ጊዜ “ይህ ነገር ምን ይሆን?” በማለት ግራ ተጋቡ። 25በዚህ ጊዜ አንድ ሰው መጣና “በወህኒ ቤት ያስገባችኋቸው ሰዎች እነሆ፥ በቤተ መቅደስ ቆመው ሕዝቡን ያስተምራሉ” ብሎ ነገራቸው። 26ወዲያውኑ የቤተ መቅደሱ የዘበኞች አለቃና ሎሌዎቹ ሄደው አመጡአቸው፤ ያመጡአቸውም በኀይል ሳይሆን በማግባባት ነው፤ ይህንንም ያደረጉት ሕዝቡ በድንጋይ እንዳይወግራቸው በመፍራት ነው።
27አምጥተውም በሸንጎው ፊት አቆሙአቸው፤ የካህናት አለቃውም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፤ 28“የኢየሱስን ስም በመጥራት እንዳታስተምሩ በጥብቅ አዘናችሁ ነበር፤ ነገር ግን እነሆ፥ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞላችኋት፤ እናንተ ለዚያ ሰው ሞት እኛን ተጠያቂዎች ልታደርጉን ትፈልጋላችሁ።” #ማቴ. 27፥25።
29ጴጥሮስና ሌሎች ሐዋርያት ግን እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ለሰው ከመታዘዝ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ይገባናል፤ 30የአባቶቻችን አምላክ እናንተ በእንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን ከሞት አስነሣው፤ 31እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ንስሓንና የኃጢአትን ይቅርታ እንዲሰጥ ኢየሱስን መሪና አዳኝ አድርጎ በቀኙ በክብር እንዲቀመጥ አድርጎታል፤ 32ስለዚህ ነገር እኛ ምስክሮች ነን፤ እግዚአብሔር ለሚታዘዙት ሁሉ የሰጣቸው መንፈስ ቅዱስም ምስክር ነው።”
33የሸንጎ አባሎች ይህን በሰሙ ጊዜ በጣም ተቈጥተው ሐዋርያቱን ለመግደል ፈለጉ። 34ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ የተከበረና የሕግ መምህር የሆነ፥ ገማልያል የተባለ አንድ ፈሪሳዊ የሸንጎ አባል ተነሣና ለጥቂት ጊዜ ሐዋርያቱን ገለል እንዲያደርጉአቸው አዘዘ። 35ከዚህ በኋላ የሸንጎውን አባሎች እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! በእነዚህ ሰዎች ላይ በምታደርጉት ነገር ተጠንቀቁ። 36ከዚህ በፊት ቴዎዳስ የሚባል ሰው ‘እኔ ትልቅ ሰው ነኝ’ ብሎ ተነሥቶ ነበር፤ አራት መቶ የሚያኽሉም ሰዎች ከእርሱ ጋር ተባብረው ነበር። ነገር ግን እርሱ ተገደለ፤ ተከታዮቹ ተበታተኑ፤ ዓላማውም እንዳልነበረ ሆነ። 37ከዚያም በኋላ የሕዝብ ቈጠራ በተደረገበት ዘመን ገሊላዊው ይሁዳ ተነሥቶ ብዙ ሰዎች እንዲከተሉት አድርጎ ነበር፤ እርሱም ተገደለ፤ የተከተሉትም ሁሉ ተበታተኑ። 38ስለዚህ አሁንም እኔ የምላችሁ ከነዚህ ሰዎች እንድትርቁና እንድትተዉአቸው ነው፤ ይህ አሳብ ወይም ሥራ ከሰው የመጣ ከሆነ ይጠፋል። 39ከእግዚአብሔር የመጣ ከሆነ ግን እነርሱን ልታጠፉአቸው አትችሉም፤ እንዲያውም ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት ይሆንባችኋል።” እነርሱም የገማልያልን ምክር ተቀበሉ።
40ከዚህ በኋላ ሐዋርያቱን ወደ እነርሱ ጠርተው አስገረፉአቸው፤ የኢየሱስንም ስም በመጥራት እንዳይናገሩ አዘዙአቸውና ለቀቁአቸው። 41ሐዋርያት ግን ስለ ኢየሱስ ስም ውርደት ለመቀበል የተገቡ በመሆናቸው ደስ እያላቸው ከሸንጎው ወጥተው ሄዱ፤ 42በየቀኑም በቤተ መቅደስና በየቤቱም ስለ መሲሑ ስለ ኢየሱስ ማስተማርንና የምሥራች መናገርን አላቋረጡም ነበር።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Video for የሐዋርያት ሥራ 5