YouVersion Logo
Search Icon

የሐዋርያት ሥራ 6

6
ሰባት ዲያቆናት መመረጣቸው
1ከጥቂት ጊዜ በኋላ የአማኞች ቊጥር እየበዛ ሲሄድ የግሪክ ቋንቋ የሚናገሩ አይሁድ የይሁዳ አገር ተወላጆች በሆኑት አይሁድ ላይ ማጒረምረም ጀመሩ፤ ያጒረመረሙትም በየቀኑ ይታደል በነበረው ርዳታ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች ችላ ይሉባቸው ስለ ነበር ነው። 2ስለዚህ ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አማኞችን ሁሉ ሰብስበው እንዲህ አሉአቸው፦ “ምግብ ለማደል ብለን የእግዚአብሔርን ቃል የማስተማር ሥራችንን መተው አይገባንም። 3እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፥ በመልካም ጠባያቸው የተመሰገኑ፥ በመንፈስ ቅዱስና በጥበብ የተሞሉ ሰባት ሰዎችን ከመካከላችሁ ምረጡ፤ እነርሱን ለዚህ ኀላፊነት እንሾማቸዋለን። 4እኛ ግን በመጸለይና የእግዚአብሔርን ቃል በማስተማር እንተጋለን።”
5ይህ አባባል ሁሉንም አስደሰተ ቀጥሎ ያሉትም ሰዎች ተመረጡ፤ እነርሱም በእምነትና በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ እስጢፋኖስን፥ ፊልጶስ፥ ጵሮኮሮስ፥ ኒቃሮና፥ ጢሞና፥ ጰርሜና የአይሁድን እምነት ተቀብሎ የነበረው የአንጾኪያው ኒቆላዎስ ናቸው። 6እነዚህን በሐዋርያት ፊት አቆሙአቸው፤ ሐዋርያትም ከጸለዩ በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው።
7በዚህ ሁኔታ የእግዚአብሔር ቃል እየተስፋፋ ስለ ሄደ፥ በኢየሩሳሌም የአማኞች ቊጥር በጣም እየበዛ ሄደ፤ ከካህናትም እጅግ ብዙዎቹ አመኑ።
የዲያቆኑ እስጢፋኖስ መያዝ
8እስጢፋኖስ በጸጋና በኀይል ተሞልቶ ድንቅ ነገሮችንና ታላላቅ ተአምራትን በሕዝቡ መካከል ያደርግ ነበር፤ 9በዚያን ጊዜ “የነጻ ወጪዎች ምኵራብ” ከተባለው የአይሁድ ጸሎት ቤት ሰዎች፥ ከቀሬናና ከእስክንድርያ ሰዎች፥ ከኪልቅያና ከእስያ አንዳንድ ሰዎች ተነሥተው እስጢፋኖስን በመቃወም ይከራከሩት ነበር። 10ነገር ግን እስጢፋኖስ ይናገርበት የነበረውን ጥበብና መንፈስ መቋቋም አልቻሉም። 11በዚያን ጊዜ “ይህ ሰው በሙሴና በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ሲናገር ሰምተነዋል” የሚሉ ሰዎችን በስውር አነሣሡበት። 12በዚሁ ዐይነት ሕዝቡንና ሽማግሌዎቹን የሕግ መምህራንንም በእርሱ ላይ አነሣሡ፤ ወደ እስጢፋኖስም ሄዱና ይዘው በሸንጎው ፊት አቀረቡት። 13በእርሱ ላይ በሐሰት የሚመሰክሩ አንዳንድ ሰዎችንም አመጡ፤ የሐሰት ምስክሮችም እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሰው በዚህ ቤተ መቅደስና በሕግ ላይ የስድብ ቃል ከመናገር አይቈጠብም። 14ደግሞም ‘ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ቤተ መቅደስ ያፈርሳል፤ ሙሴም ያስተላለፈልንን ሥርዓት ይለውጣል’ ብሎ ሲናገር ሰምተነዋል።” 15በዚህ ጊዜ በሸንጎው የተገኙት ሁሉ እስጢፋኖስን ትኲር ብለው ሲመለከቱት ፊቱ እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ታያቸው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Video for የሐዋርያት ሥራ 6