ወደ ገላትያ ሰዎች 1
1
1በሰዎች ወይም በሰው አማካይነት ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስና እርሱንም ከሞት ባስነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ ሆኜ ከተላክሁ ከእኔ ከጳውሎስ፥ 2ከእኔም ጋር ካሉት ወንድሞች ሁሉ ለገላትያ አብያተ ክርስቲያን የተላከ።
3ከአባታችን ከእግዚአብሔር፥ ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
4ከዚህ ከክፉ ዘመን ያድነን ዘንድ በአምላካችንና በአባታችን ፈቃድ ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ። 5ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን! አሜን።
እውነተኛው ወንጌል አንድ ብቻ ስለ መሆኑ
6በክርስቶስ ጸጋ ከጠራችሁ አምላክ እንዲህ ፈጥናችሁ መለየታችሁና ወደ ሌላ ወንጌል ማዘንበላችሁ ያስደንቀኛል። 7ይህንንም ያልኩት ግራ የሚያጋቡአችሁና የክርስቶስንም ወንጌል ለማጣመም የሚፈልጉ አንዳንድ ሰዎች ስላሉ ነው እንጂ ወንጌልማ በመሠረቱ አንድ ብቻ ነው። 8ይሁን እንጂ እኛም ብንሆን፥ ወይም የሰማይ መልአክ እንኳ ቢሆን፥ እኛ ከሰበክንላችሁ የተለየ ሌላ ወንጌል ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን! 9ከዚህ በፊት እንዳልኩት አሁንም ደግሜ እላለሁ፤ እናንተ ከተቀበላችሁት የተለየ ሌላ ወንጌል ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን!
10ታዲያ፥ እኔ የምፈልገው ሰው እንዲያመሰግነኝ ነውን? ወይስ እግዚአብሔር እንዲያመሰግነኝ? ወይስ ሰውን ደስ ለማሰኘት የምፈልግ መስሎአችሁ ይሆን? ሰዎችን ለማስደሰት የምፈልግ ብሆን ኖሮ የክርስቶስ አገልጋይ ባልሆንኩም ነበር።
የጳውሎስ ለሐዋርያነት መጠራት
11ወንድሞቼ ሆይ! እኔ የሰበክሁላችሁ ወንጌል ከሰው የተገኘ አለመሆኑን እንድታውቁ እፈልጋለሁ። 12ይህን ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ ገለጠልኝ እንጂ ከማንም ሰው አልተቀበልኩትም፤ ወይም ማንም ሰው አላስተማረኝም።
13ቀድሞ የአይሁድ እምነት ተከታይ በነበርኩበት ጊዜ እንዴት እንደ ኖርኩ ሰምታችኋል፤ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ከመጠን በላይ እያሳደድኩ ለማጥፋት እጥር ነበር። #ሐ.ሥ. 8፥3፤ 22፥4-5፤ 26፥9-11። 14የአይሁድን እምነት በመጠበቅ በዘመኔ ከነበሩት ከብዙዎቹ አይሁድ ወገኖቼ ሁሉ እበልጥ ነበር፤ ስለ አባቶችም ወግ ከፍተኛ ቅናት ነበረኝ። #ሐ.ሥ. 22፥3።
15ነገር ግን ከመወለዴ በፊት እግዚአብሔር መረጠኝ፤ በጸጋውም ጠራኝ። 16ለአሕዛብ ስለ ልጁ የምሥራቹን ቃል እንዳበሥር እግዚአብሔር ልጁን ሊገልጥልኝ በወደደ ጊዜ እኔ ከማንም ጋር አልተማከርኩም፤ #ሐ.ሥ. 9፥3-6፤ 22፥6-10፤ 26፥13-18። 17ወይም ከእኔ በፊት ሐዋርያት የነበሩትን ለመገናኘት ወደ ኢየሩሳሌም አልሄድኩም፤ ነገር ግን አስቀድሜ ወደ ዐረብ አገር ሄድኩ፤ እንደገናም ወደ ደማስቆ ተመለስኩ። 18ቀጥሎም ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋ የሚባለውን ጴጥሮስን ለማየት ወደ ኢየሩሳሌም ሄድኩ፤ እዚያም ከእርሱ ጋር ዐሥራ አምስት ቀን ቈየሁ። #ሐ.ሥ. 9፥26-30። 19የጌታን ወንድም ያዕቆብን አየሁ እንጂ ከሌሎቹ ከሐዋርያት ማንንም አላየሁም።
20ይህ የምጽፍላችሁ ሐሰት እንዳልሆነ በእግዚአብሔር ፊት አረጋግጥላችኋለሁ።
21ከዚህ በኋላ ወደ ሶርያና ወደ ኪልቅያ አገር ሄድኩ። 22በይሁዳ ምድር ያሉት የክርስቶስ አብያተ ክርስቲያን እኔን ፊት ለፊት አይተው ገና አላወቁኝም ነበር። 23እነርሱ የሰሙት “ያ ቀድሞ ያሳድደን የነበረ ሰው ያን ሊያጠፋው ይፈልግ የነበረውን እምነት አሁን ይሰብካል” የሚል ቃል ነበር። 24በእኔ ምክንያትም እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር።
Currently Selected:
ወደ ገላትያ ሰዎች 1: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997