YouVersion Logo
Search Icon

ወደ ገላትያ ሰዎች 2

2
የጳውሎስ ሐዋርያነት በሌሎች ሐዋርያት ዘንድ መታወቁ
1ከዐሥራ አራት ዓመት በኋላ ከበርናባስ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሼ ሄድኩ፤ ቲቶንም ከእኔ ጋር ይዤው ሄጄ ነበር። #ሐ.ሥ. 11፥30፤ 15፥2። 2የሄድኩትም እግዚአብሔር በገለጠልኝ መሠረት ነው። ከዚህ በፊት የሠራሁትም ሆነ አሁን የምሠራው ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር በማለት ለአሕዛብ የምሰብከውን ወንጌል ታላላቅ ለሆኑት መሪዎች በግል አስታወቅኋቸው። 3ከእኔ ጋር የነበረው ቲቶ ምንም እንኳ ግሪካዊ ቢሆን እንዲገረዝ አልተገደደም። 4ነገር ግን በመካከላችን ሾልከው በስውር የገቡ አንዳንድ ሐሰተኞች ወንድሞች እንዲገረዝ ፈልገው ነበር፤ እነዚህ ሰዎች ለስለላ በመካከላችን ሠርገው የገቡት በኢየሱስ ክርስቶስ ያለንን ነጻነት ነጥቀው ወደ ባሪያነት ሊመልሱን አስበው ነው። 5እኛ ግን የወንጌል እውነት በእናንተ ዘንድ ጸንቶ እንዲኖር በማለት ለጥቂት ጊዜ እንኳ አልተበገርንላቸውም።
6እነዚህ መሪዎች መስለው የሚታዩት ግን እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ ስለማያዳላ ስለ እነርሱ የቀድሞ ማንነት ግድ የለኝም፤ እነዚህ መሪዎች የተባሉት እኔ በማበሥረው የምሥራች ቃል ላይ ምንም አዲስ ነገር አልጨመሩም። #ዘዳ. 10፥17። 7እንዲያውም እግዚአብሔር ጴጥሮስን ለአይሁድ የምሥራቹን ቃል እንዲያበሥር በተላከው ዐይነት እኔንም የምሥራቹን ቃል ለአሕዛብ እንዳበሥር እንዳደረገኝ ተገነዘቡ፤ 8ስለዚህ ጴጥሮስን የአይሁድ ሐዋርያ ሆኖ እንዲያገለግል ያደረገው አምላክ እኔንም የአሕዛብ ሐዋርያ ሆኜ እንዳገለግል አድርጎኛል። 9እንደ ምሰሶ መስለው የሚታዩት መሪዎች ያዕቆብና ጴጥሮስ ዮሐንስም እግዚአብሔር በጸጋ ይህን ልዩ የአገልግሎት ዕድል እንደ ሰጠኝ በተረዱ ጊዜ ለእኔና ለበርናባስ የመተባበራቸው ምልክት የሆነውን ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤ እኛ ወደ አሕዛብ እንድንሄድ እነርሱም ወደ አይሁድ እንዲሄዱ ተስማሙ። 10ብቻ በመካከላቸው ያሉትን ድኾች እንድናስታውስ ዐደራ አሉን፤ ይህም እኔ በትጋት ያደረግኹት ነገር ነው።
ጳውሎስ በአንጾኪያ ጴጥሮስን እንደ ተቃወመው
11ጴጥሮስ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ በግልጥ ተሳስቶ ስለ ነበር ፊት ለፊት ተቃወምኩት፤ 12ያዕቆብ የላካቸው አንዳንድ ሰዎች ወደ አንጾኪያ ከመምጣታቸው በፊት ከአሕዛብ መካከል ከአመኑት ጋር አብሮ ይበላ ነበር፤ እነርሱ ከመጡ በኋላ ግን “ከአሕዛብ ወገን ያመኑት መገረዝ አለባቸው” የሚሉትን ቡድኖች በመፍራት ወደ ኋላ አፈግፍጎ ከአሕዛብ ተለየ። 13አንዳንድ ከአይሁድ ወገን የሆኑ ክርስቲያኖችም የጴጥሮስን ግብዝነት ተከተሉ፤ በርናባስ እንኳ ሳይቀር በግብዝነታቸው ተስቦ ነበር። 14የእነርሱ አድራጎት ከወንጌል እውነት ጋር አለመስማማቱን ባየሁ ጊዜ ጴጥሮስን “አንተ አይሁዳዊ ሆነህ ሳለ በአይሁድ ሥርዓት ሳይሆን በአሕዛብ ሥርዓት ትኖር ነበር። ታዲያ፥ አሕዛብ በአይሁድ ሥርዓት እንዲኖሩ ለምን ታስገድዳቸዋለህ?” ስል በሁሉም ፊት ተቃወምኩት።
አይሁድም ሆኑ አሕዛብ የሚድኑት በእምነት መሆኑ
15በእርግጥ እኛ በትውልዳችን አይሁድ ነን፤ እንደ ኃጢአተኞች አሕዛብም አይደለንም። 16ነገር ግን ሰው የሚጸድቀው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንጂ ሕግን በመፈጸም እንዳልሆነ እናውቃለን፤ እኛም ሕግን በመፈጸም ሳይሆን በክርስቶስ በማመን እንድንጸድቅ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነናል፤ ማንም ሰው የኦሪትን ሕግ በመፈጸም አይጸድቅም። #መዝ. 143፥2፤ ሮም 3፥20፤22። 17በክርስቶስ በማመን ለመጽደቅ ስንፈልግ እኛ ራሳችን ኃጢአተኞች ሆነን ብንገኝ ታዲያ፥ ኃጢአት እንድንሠራ የሚያደርገን ክርስቶስ ነው ማለት ነውን? ከቶ አይደለም! 18እኔ ራሴ ያፈረስኩትን የሕግ ሥርዓት መልሼ የምሠራው ከሆንኩ እኔው ራሴ ሕግ አፍራሽ መሆኔን አረጋግጣለሁ ማለት ነው። 19ለእግዚአብሔር እኖር ዘንድ በሕግ አማካይነት በሞት የመለየትን ያኽል ከሕግ ተለይቼአለሁ። 20እኔ ከክርስቶስ ጋር እንደ ተሰቀልኩ ያኽል ስለምቈጥር ከእንግዲህ ወዲህ ክርስቶስ በእኔ ውስጥ ይኖራል እንጂ እኔ ለራሴ ሕይወት የምኖር አይደለሁም፤ አሁንም በሥጋዊ አካሌ የምኖረው በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ በማመን በተገኘው ሕይወት ነው። 21የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ አላስቀርም፤ ሰው የሚጸድቀው ሕግን በመፈጸም ከሆነ ክርስቶስ የሞተው በከንቱ ነው ማለት ነው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in