YouVersion Logo
Search Icon

ወደ ገላትያ ሰዎች 3

3
ጽድቅ የሚገኘው በክርስቶስ በማመን መሆኑ
1እናንተ ሞኞች የገላትያ ሰዎች! ማን አፍዝ አደንግዝ አደረገባችሁ? ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ ተሰቅሎ በፊት ለፊታችሁ በግልጥ ይታይ ነበር። 2ማወቅ የምፈልገው ይህን ብቻ ነው፤ ለመሆኑ እናንተ መንፈስ ቅዱስን የተቀበላችሁት ሕግን በመፈጸም ነውን? ወይስ የምሥራቹን ቃል ሰምታችሁ በማመን ነው? 3እናንተ በእግዚአብሔር መንፈስ ጀምራችሁ አሁን በሥጋዊ ጥረት መፈጸም ትፈልጋላችሁ፤ ለካ እስከዚህ ድረስ ሞኞች ናችሁ! 4በወንጌል ምክንያት የተቀበላችሁት መከራ ሁሉ ከንቱ ሆኖ ቀረ ማለት ነውን? ይህን አድርጋችሁ ከሆነ በእርግጥ ከንቱ ሆኖ ቀርቶአል። 5እግዚአብሔር መንፈሱን የሚሰጣችሁና በእናንተ ዘንድ ተአምራትን የሚያደርገው ሕግን በመፈጸማችሁ ነውን? ወይስ የምሥራቹን ቃል ሰምታችሁ በማመናችሁ ነው?
6ይህም “አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፤ እምነቱም ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። #ዘፍ. 15፥6፤ ሮም 4፥3። 7እንግዲህ የሚያምኑ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ ዕወቁ። #ሮም 4፥16። 8እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንደሚያጸድቅ ቅዱስ መጽሐፍ አስቀድሞ አይቶ “ሕዝቦች ሁሉ በአንተ ይባረካሉ” በማለት አስቀድሞ ለአብርሃም የምሥራቹን ቃል አብሥሮአል። #ዘፍ. 12፥3። 9ስለዚህ የሚያምኑ ሁሉ ከአመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ።
10“በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ትእዛዞች ሁሉ ጸንቶ የማይኖርና የማይፈጽማቸው ሁሉ የተረገመ ነው” ተብሎ ስለ ተጻፈ “ሕግን በመፈጸም እንጸድቃለን” የሚሉ ሁሉ የተረገሙ ናቸው። #ዘዳ. 27፥26። 11“ጻድቅ ሰው ግን በእምነት ሕይወትን ያገኛል” ተብሎ ስለ ተጻፈ ሕግን በመፈጸም ማንም ሰው በእግዚአብሔር ፊት እንደማይጸድቅ ግልጥ ነው። #ዕን. 2፥4። 12ሕግ በእምነት ላይ የተመሠረተ አይደለም፤ እንዲያውም “ሰው በሕግ ሊኖር የሚችለው የሕግ ትእዛዞችን ሁሉ ሲፈጽም ነው” ተብሎ ተጽፎአል። #ዘሌ. 18፥5።
13“በእንጨት ላይ ተሰቅሎ የሚሞት ሁሉ የተረገመ ነው” ተብሎ ስለ ተጻፈ ክርስቶስ ስለ እኛ እንደ ተረገመ ሰው ሆኖ ሕግ ከሚያስከትለው ርግማን ዋጀን። #ዘዳ. 21፥23። 14ይህም የሆነው እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠው በረከት በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ለአሕዛብ እንዲደርስና እኛም እግዚአብሔር እሰጣችኋለሁ ያለውን መንፈስ ቅዱስን በእምነት እንድንቀበል ነው።
ሕግ የተስፋውን ቃል የማይሽር መሆኑ
15ወንድሞቼ ሆይ! እስቲ ይህን ነገር በሰው ዘንድ ከተለመደ ነገር ጋር አነጻጽሩት፤ አንድ ሰው የገባው ቃል ኪዳን እንኳ ከጸደቀ በኋላ ማንም ሰው ሊሽረው ወይም ሊጨምርበት አይችልም። 16እግዚአብሔርም ለአብርሃምና ለዘሩ የተስፋ ቃል የሰጠው በዚህ ዐይነት ነው፤ መጽሐፍ የተስፋ ቃል ከአብርሃም በኋላ የተሰጠው ለብዙዎች እንደ ሆነ አድርጎ “ለዘሮችህ” አይልም፤ ነገር ግን ለአንድ እንደ ሆነ አድርጎ “ለዘርህ” ይላል፤ ይህም “ዘርህ” የተባለው ክርስቶስ ነው። #ዘፍ. 12፥7። 17እንግዲህ እኔ የምለው ይህን ነው፤ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የተሰጠው ሕግ ቀደም ብሎ በእግዚአብሔር ተረጋግጦ የተሰጠውን ቃል ኪዳን በመሻር የተስፋውን ቃል ሊያጠፋው አይችልም። 18አንድ ነገር የሚወረሰው በሕግ አማካይነት ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር በሰጠው የተስፋ ቃል አማካይነት መሆኑ በቀረ ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ውርስን ለአብርሃም የሰጠው በተስፋው ቃል አማካይነት ነው። #ሮም 4፥14።
19ታዲያ፥ ሕግ የተሰጠው ለምንድን ነው? ሕግ የተጨመረው ለአብርሃም በተስፋ የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ ክፉ ሥራ ምን መሆኑን ለማመልከት ነው፤ ሕጉ በሥራ ላይ የዋለው በመላእክት ተሰጥቶ በአንድ ሰው አማካይነት ነው። 20ይሁን እንጂ በመካከል ሆኖ የሚያስታርቅ ሰው ለሁለት ወገን ነው እንጂ ለአንድ ወገን ብቻ አይሠራም፤ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።
ሕግ ለምን እንደ ተሰጠ
21እንግዲህ ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ይቃወማልን? ከቶ አይቃወምም! ሕይወት የሚገኝበት ሕግ ተሰጥቶ ቢሆን ኖሮ ጽድቅ በሕግ አማካይነት በተገኘ ነበር። 22ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የተስፋ ቃል ለሚያምኑ እንዲሰጥ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚለው ዓለም በሙሉ ለኃጢአት በመገዛት የኃጢአት እስረኛ ሆኖአል።
23እምነት ከመምጣቱ በፊት የሕግ እስረኞች ነበርን፤ ይህም እምነት እስከሚገለጥበት ጊዜ ድረስ በሕግ ጥበቃ ሥር ነበርን። 24በዚህ ዐይነት በእምነት እንድንጸድቅ ክርስቶስ እስኪመጣ ሕግ ሞግዚታችን ሆኖ ነበር። 25አሁን ግን እምነት ስለ መጣ በሕግ ሞግዚትነት ሥር መሆናችን ቀርቶአል።
26በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ሁላችሁም የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ፤ 27በጥምቀት ከክርስቶስ ጋር አንድ የሆናችሁ ሁሉ ክርስቶስን እንደ ልብስ ለብሳችሁታል። 28ሁላችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ስለ ሆናችሁ በአይሁዳዊና በግሪካዊ፥ በአገልጋይና በጌታ፥ በወንድና በሴት መካከል ምንም ልዩነት የለም። 29እንግዲህ የክርስቶስ ከሆናችሁ የአብርሃም ዘር ናችሁ፤ በተስፋውም ቃል መሠረት ወራሾች ናችሁ። #ሮም 4፥13።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in