YouVersion Logo
Search Icon

ወደ ዕብራውያን የተላከ መልእክት 3

3
ኢየሱስ ከሙሴ የሚበልጥ ስለ መሆኑ
1ስለዚህ ለሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ የተቀደሳችሁ ምእመናን ሆይ! የእምነታችን ሐዋርያና የካህናት አለቃ ኢየሱስን አስቡ። 2ሙሴ በእግዚአብሔር ቤት ሁሉ ታማኝ እንደ ነበረ ኢየሱስም ለሾመው ለእግዚአብሔር ታማኝ ነበር። 3ቤትን የሚሠራ ከቤቱ ይልቅ የበለጠ ክብር እንዳለው ሁሉ ኢየሱስም ከሙሴ ይልቅ የበለጠ ክብር ይገባዋል። #ዘኍ. 12፥7። 4በእርግጥ ለእያንዳንዱ ቤት ሠሪ አለው፤ ሁሉን ነገር የሠራ ግን እግዚአብሔር ነው። 5ወደፊት መባል ለሚገባው ነገር ምስክር እንዲሆን ሙሴ በመላው በእግዚአብሔር ቤት እንደ አገልጋይ ታማኝ ነበር። 6ክርስቶስ ግን በእግዚአብሔር ቤት ታማኝ የሆነው እንደ ልጅ ሆኖ ነው፤ ቤቱም እኛ ነን፤ ቤቱ የምንሆነውም የምንተማመንበትን ነገርና የምንመካበትን ተስፋ አጽንተን ስንይዝ ነው።
ለእግዚአብሔር ሕዝብ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
7ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሚለው
“ዛሬ ድምፁን ስትሰሙ #መዝ. 95፥7-11።
8በበረሓ በተፈታተናችሁኝ ጊዜ እንዳመፃችሁት ዐይነት
ልባችሁን እምቢተኛ አታድርጉ፤
9እዚያ አባቶቻችሁ ተፈታተኑኝ፤ ተገዳደሩኝም፤
አርባ ዓመት ያደረግኹትንም አዩ” ይላል እግዚአብሔር።
10“ስለዚህ ያንን ትውልድ ተቈጥቼ፥
‘ልባቸው ዘወትር ይሳሳታል፤
መንገዴንም አላወቁም’ አልኩ።”
11ደግሞም፥
“ ‘እኔ ወደምሰጣቸው የዕረፍት ቦታ ከቶ አይገቡም!’ ብዬ
በቊጣዬ ምዬአለሁ።”
12ወዳጆቼ ሆይ፥ ከእናንተ መካከል ማንም ከሕያው እግዚአብሔር የሚያርቅ ክፉና የማያምን ልብ እንዳይኖረው ተጠንቀቁ። 13ይልቅስ ከእናንተ በኃጢአት ተታሎ ልቡን እምቢተኛ እንዳያደርግ “ዛሬ” ተብሎ የተጠራው ጊዜ እስካለ ድረስ በየቀኑ ተመካከሩ። 14በመጀመሪያ የነበረንን እምነታችንን እስከ መጨረሻ አጽንተን ከያዝን ከክርስቶስ ጋር ወራሾች እንሆናለን።
15ይህም “ዛሬ ድምፁን ስትሰሙ
በዚያ በዐመፃው ጊዜ እንዳደረጋችሁት ዐይነት ልባችሁን እምቢተኛ አታድርጉ”
ተብሎ እንደ ተነገረው ነው።
16ለመሆኑ እነዚያ ድምፁን ከሰሙ በኋላ ያመፁ እነማን ነበሩ? እነርሱ ሙሴ እየመራቸው ከግብጽ የወጡት ሁሉ አልነበሩምን? 17እግዚአብሔርን አርባ ዓመት ሙሉ ሲያስቈጡት የኖሩ እነማን ነበሩ? እነዚያ ኃጢአት የሠሩና ሬሳቸው በበረሓ ወድቆ የቀረው አይደሉምን? 18ደግሞስ እነዚያን ያልታዘዙትን ካልሆነ በቀር “ወደ ዕረፍቴ አትገቡም” ብሎ የማለባቸው እነማን ነበሩ? 19እንግዲህ ሊገቡ ያልቻሉት ባለማመናቸው ምክንያት መሆኑን እናያለን።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in