YouVersion Logo
Search Icon

የዮሐንስ ወንጌል 16

16
1“እነሆ፥ ይህን ሁሉ የነገርኳችሁ እምነታችሁ እንዳይናወጥ ብዬ ነው። 2ከምኲራቦች አስወጥተው ያባርሩአችኋል፤ እንዲያውም እናንተን የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን የሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል። 3ይህንንም የሚያደርጉት አብንም ሆነ እኔን ስላላወቁ ነው። 4ይህንን ለእናንተ መናገሬ ግን ጊዜው ሲደርስ ምን እንዳልኳችሁ እንድታስታውሱ ነው።”
የመንፈስ ቅዱስ ሥራ
“ይህን ሁሉ ከአሁን በፊት ያልነገርኳችሁ ከእናንተ ጋር ስለ ነበርኩ ነው፤ 5አሁን ግን ወደ ላከኝ መሄዴ ነው፤ ሆኖም ከእናንተ ‘ወዴት ትሄዳለህ?’ ብሎ የሚጠይቀኝ የለም። 6ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ ስለ ነገርኳችሁ ልባችሁ በሐዘን ተሞልቶአል። 7እኔ ግን እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ የእኔ መሄድ ለእናንተ ይጠቅማችኋል፤ እኔ ካልሄድኩ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣም፤ እኔ ከሄድኩ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ። 8እርሱ በመጣ ጊዜ ስለ ኃጢአት፥ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድም ምክንያት የዓለምን ሰዎች ያጋልጣል። 9ስለ ኃጢአት የሚያጋልጠው በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ 10ስለ ጽድቅ የሚያጋልጠው ወደ አብ ስለምሄድና ከእንግዲህ ወዲህ ስለማታዩኝ ነው፤ 11ስለ ፍርድ የሚያጋልጠው የዚህ ዓለም ገዢ ስለ ተፈረደበት ነው።
12“ገና የምነግራችሁ ብዙ ነገር አለኝ፤ ነገር ግን አሁን ይከብዳችኋል፤ 13የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል። እርሱ የሚናገረው የሰማውን እንጂ የራሱን ስላልሆነ እርሱ ወደፊት የሚሆኑትን ነገሮች ይነግራችኋል። 14የእኔ ከሆነው ወስዶ ስለሚነግራችሁ እኔን ያከብረኛል። 15የአብ የሆነው ሁሉ የእኔ ነው፤ ‘የእኔ ከሆነው ወስዶ ይነግራችኋል’ ያልኳችሁ ስለዚህ ነው።
የሐዘናችሁ ወደ ደስታ መለወጥ
16“ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ እንደገናም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ታዩኛላችሁ።”
17ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶች፥ “ይህ፥ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ደግሞ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ታዩኛላችሁ፤ ደግሞ ወደ አብ እሄዳለሁ’ የሚለን ነገር ምንድን ነው?” ተባባሉ። 18“እንግዲህ ይህ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ’ የሚለው ነገር ምንድን ነው? የሚናገረውን ነገር አናውቅም” በመባባል መላልሰው ተጠያየቁ።
19ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደ ፈለጉ ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እርስ በርሳችሁ የምትጠያየቁ፥ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ደግሞም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ታዩኛላችሁ’ ስላልኳችሁ ነውን? 20እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ ታለቅሳላችሁ፤ ትጮኻላችሁም፤ ዓለም ግን ደስ ይለዋል፤ እናንተ ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን ሐዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል። 21ሴት በምትወልድበት ጊዜ የምጥ ቀንዋ ስለ ደረሰ ታዝናለች፤ ከወለደች በኋላ ግን በዓለም ላይ ሕፃን ስለ ተወለደ ከመደሰትዋ የተነሣ ጭንቀትዋን አታስታውሰውም። 22እንዲሁም እናንተ አሁን ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን እኔ እንደገና አያችኋለሁ፤ ልባችሁም ደስ ይለዋል፤ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም።
23“በዚያን ቀን ከእኔ ምንም አትለምኑም፤ እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ አብን በስሜ ብትለምኑት ሁሉን ነገር ይሰጣችኋል። 24እስከ አሁን በስሜ ምንም ነገር አለመናችሁም፤ ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ደስታችሁም ፍጹም ይሆናል።
25“እስከ አሁን በምሳሌ ነገርኳችሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ በምሳሌ የማልናገርበት ጊዜ ይመጣል፤ ነገር ግን ስለ አብ ሁሉን ነገር ገልጬ እነግራችኋለሁ። 26በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ‘አብን እለምንላችኋለሁ’ አልላችሁም። 27ምክንያቱም አብ ራሱ ስለሚወዳችሁ ነው፤ አብም የሚወዳችሁ እኔን ስለ ወደዳችሁኝና ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣሁ ስላመናችሁ ነው። 28ከአብ ዘንድ ወጥቼ፥ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ እንደገናም ይህን ዓለም ትቼ፥ ወደ አብ እሄዳለሁ።”
29ደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አሉ፤ “እነሆ! አሁን በምሳሌ ሳይሆን በግልጥ ተናገርክ፤ 30አንተ ሁሉን እንደምታውቅና ማንም ጥያቄ ሊያቀርብልህ እንደማያስፈልግህ አሁን ዐወቅን፤ ስለዚህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ወጣህ እናምናለን።”
31ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “አሁንስ አምናችኋል? 32ይሁን እንጂ እያንዳንዳችሁ በየበኩላችሁ የምትበታተኑበትና እኔን ብቻዬን የምትተዉበት ሰዓት ይመጣል፤ ሰዓቱም አሁን ደርሶአል፤ ነገር ግን አብ ከእኔ ጋር ስለ ሆነ ብቻዬን አይደለሁም። 33ይህን ለእናንተ መናገሬ በእኔ ሆናችሁ ሰላም እንዲኖራችሁ ብዬ ነው፤ በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፥ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in