መጽሐፈ መዝሙር 37
37
የክፉዎችና የደጎች መጨረሻ ዕድል
1በክፉዎች ምክንያት አትበሳጭ፤
ኃጢአት በሚሠሩም አትቅና።
2እንደ ሣር ቶሎ ይደርቃሉ፤
እንደ ቅጠልም ጠውልገው ይረግፋሉ።
3በእግዚአብሔር ታምነህ መልካምን አድርግ፤
በምድሪቱም በሰላም ትኖራለህ።
4በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፤
እርሱም የልብህን ፍላጎት ሁሉ ይሰጥሃል።
5አካሄድህን ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤
በእርሱ ታመን፤ እርሱም ይረዳሃል።
6ጽድቅህን እንደ ብርሃን
የጉዳይህንም ትክክለኛነት
እንደ ቀትር ፀሐይ ያበራዋል።
7በትዕግሥት ጸንተህ
እግዚአብሔር የሚያደርገውን ለማየት ተጠባበቅ፤
ሌሎች ሰዎች ክፉ ሐሳባቸው ቢሳካላቸው አትበሳጭ።
8ቊጣ ወደ ክፉ ነገር ስለሚያመራ።
ራስህን ከቊጣ መልስ፤ ከንዴትም ተጠበቅ፤
9ክፉ አድራጊዎች ይገደላሉ፤
በእግዚአብሔር የሚታመኑ ግን ምድርን ይወርሳሉ።
10ከጥቂት ጊዜ በኋላ ክፉ አድራጊዎች ፈጥነው ይጠፋሉ፤
ብትፈልጋቸው እንኳ አታገኛቸውም።
11ትሑቶች ምድርን ይወርሳሉ፤
ብልጽግናንና ሰላምን በማግኘት ይደሰታሉ። #ማቴ. 5፥5።
12ክፉ ሰው ደጉን ሰው ለማጥፋት ያሳድምበታል፤
በጥላቻም ጥርሱን ያፋጭበታል።
13ክፉዎች ሰዎች የሚጠፉበት ቀን እንደ ተቃረበ ስለሚያውቅ
እግዚአብሔር በእነርሱ ይስቃል።
14ክፉዎች፥ ድኾችንና ምስኪኖችን ለመግደል፥
ደግ ሥራ የሚሠሩትንም ለማረድ፥
ሰይፋቸውን ይመዛሉ፤ ቀስታቸውን ያዘጋጃሉ።
15ነገር ግን ሰይፋቸው የራሳቸውን ልብ ይወጋል፤
ቀስታቸውም ይሰበራል።
16ከክፉ ሰው ብዙ ሀብት ይልቅ፥
የደግ ሰው ጥቂት ሀብት ይበልጣል።
17የክፉዎች ኀይል ይሰበራል
ጻድቃንን ግን እግዚአብሔር ያበረታቸዋል።
18እግዚአብሔር ታዛዦቹን በየቀኑ ይጠብቃቸዋል፤
የሰጣቸውም ስጦታ ለዘለዓለም ከእነርሱ ጋር ይኖራል።
19ክፉ ቀን ሲመጣ ችግር አይደርስባቸውም፤
በራብ ዘመንም በቂ ምግብ በማግኘት ይጠግባሉ።
20ክፉዎች ግን ይጠፋሉ፤
የእግዚአብሔር ጠላቶች እንደ በረሓ አበባ ይረግፋሉ፤
እንደ ጢስም ከዓይን ይሰወራሉ።
21ክፉ ሰው የተበደረውን አይመልስም፤
ደግ ሰው ግን በልግሥና ይሰጣል።
22እግዚአብሔር የባረካቸው ምድርን ይወርሳሉ፤
እግዚአብሔር የረገማቸው ግን ይጠፋሉ።
23እግዚአብሔር በሰው አካሄድ ከተደሰተ
የእርምጃውን ትክክለኛነት ያረጋግጥለታል።
24እግዚአብሔር በእጁ ስለሚደግፈው
ቢደናቀፍም አይወድቅም።
25ከወጣትነት እስከ ሽምግልና ኖሬአለሁ፤
ታዲያ፥ እግዚአብሔር ደጉን ሰው ሲተወው፥
ልጆቹም ምግብ አጥተው ሲለምኑ፥
ከቶ አይቼ አላውቅም።
26ደግ ሰው ሁልጊዜ በልግሥና ይሰጣል፤ እንዲሁም ያበድራል፤
ልጆቹም የተባረኩ ይሆናሉ።
27ከክፉ ነገር ራቅ፤ መልካም ነገርንም አድርግ፤
አንተም በሰላም ለዘለዓለም ትኖራለህ።
28እግዚአብሔር ትክክለኛ ፍርድን ይወዳል፤
ታማኞቹንም አይተዋቸውም፤
ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል፤
የክፉዎች ዘር ግን ይጠፋል።
29ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤
በእርስዋም ለዘለዓለም ይኖራሉ።
30ከጻድቅ ሰው አፍ ጥበብ ይወጣል፤
አንደበቱም ፍትሕን ይናገራል።
31የአምላኩም ሕግ በልቡ ነው፤
እግሩም አይደናቀፍም።
32ክፉ ሰው በጻድቁ ላይ ይሸምቃል፤
ሊገድለውም ይፈልጋል።
33እግዚአብሔር ግን በጠላቱ እጅ አሳልፎ አይሰጠውም፤
በአደባባይ ክርክርም እንዲሸነፍ አያደርገውም።
34ተስፋህን በእግዚአብሔር ላይ አድርግ፤
ትእዛዙንም ፈጽም፤
እርሱም ምድርን በማውረስ ያከብርሃል፤
ክፉዎች ሲወገዱም ታያለህ።
35አንድ ጨካኝና ክፉ ሰው በሀገሩ መሬት እንደ ለመለመ ዛፍ
ተጠናክሮ አየሁ።
36ነገር ግን ቈይቼ ብመለስ ከስፍራው አጣሁት፤
ብፈልገውም ላገኘው አልቻልኩም።
37ደጉን ሰው ተመልከት፤
ቅን የሆነውንም ሰው እይ፤
ሰላም ወዳድ ሰው ዘር ይወጣለታል።
38ኃጢአተኞች ግን ፈጽሞ ይደመሰሳሉ፤
ዘራቸውም ይጠፋል።
39የጻድቃን መዳን የሚመጣው ከእግዚአብሔር ነው፤
በችግር ጊዜ መጠጊያቸው እርሱ ነው።
40እንዲጠብቃቸው በእርሱ ስለ ተማጸኑም
ይረዳቸዋል፤ ያድናቸዋልም፤
ከክፉዎችም እጅ ይታደጋቸዋል።
Currently Selected:
መጽሐፈ መዝሙር 37: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997