የዮሐንስ ራእይ 8
8
የሰባተኛው ማኅተም መከፈት
1በጉ ሰባተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ እኩል ሰዓት ያኽል በሰማይ ዝምታ ሆነ፤ 2በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙትንም ሰባቱን መላእክት አየሁ፤ ለእነርሱ ሰባት እምቢልታዎች ተሰጡአቸው።
3የወርቅ ጥና የያዘ ሌላ መልአክ መጣና በመሠዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑ ፊት ባለው የወርቅ መሠዊያ ላይ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር የሚያቀርበው ብዙ ዕጣን ተሰጠው። #አሞጽ 9፥1፤ ዘፀ. 30፥1-3። 4የዕጣኑ ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ ወደ እግዚአብሔር ፊት ወጣ። 5ከዚህ በኋላ መልአኩ ጥናውን ይዞ ከመሠዊያው እሳት ሞላበትና ወደ ምድር ወረወረው፤ ነጐድጓድ፥ ድምፅ፥ መብረቅ፥ የምድር መናወጥም ሆነ። #ዘሌ. 16፥12፤ ሕዝ. 10፥2፤ ዘፀ. 19፥16፤ ራዕ. 11፥19፤ 16፥18።
የመለከቶቹ መነፋት
6ሰባት መለከት የያዙ ሰባቱ መላእክት መለከቶቻቸውን ለመንፋት ተዘጋጁ።
7የመጀመሪያው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በረዶና ደም የተቀላቀለበት እሳት ሆነ፤ ወደ ምድርም ተጣለ፤ የምድር ሢሶ ተቃጠለ፤ የዛፎችም ሢሶ ተቃጠለ፤ የለመለመ ሣርም ሁሉ ተቃጠለ። #ዘፀ. 9፥23-25፤ ሕዝ. 38፥22።
8ሁለተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ ትልቅ ተራራ የሚመስል ነገር እየነደደ ወደ ባሕር ተጣለ፤ የባሕር ሢሶው ደም ሆነ፤ 9በባሕር ውስጥ ከሚኖሩት ሕይወት ካላቸው ፍጥረቶች ሢሶው ሞተ፤ የመርከቦችም ሢሶ ወደመ።
10ሦስተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ እንደ ችቦ የሚቃጠል ታላቅ ኮከብ ከሰማይ ወደቀ፤ የወደቀውም በወንዞች ሢሶና በውሃ ምንጮች ላይ ነው። #ኢሳ. 14፥12። 11የኮከቡም ስም እሬቶ ይባላል፤ የውሃው አንድ ሦስተኛ መራራ ሆነ፤ መራራ በሆነውም ውሃ ጠንቅ ብዙ ሰዎች ሞቱ። #ኤር. 9፥15።
12አራተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ የፀሐይ አንድ ሦስተኛ፥ የጨረቃ አንድ ሦስተኛ፥ የኮከቦች አንድ ሦስተኛ ተመታ፤ ስለዚህ የእነርሱ አንድ ሦስተኛቸው ጨለመ፤ በዚህ ዐይነት የቀን አንድ ሦስተኛና የሌሊት አንድ ሦስተኛ ያለ ብርሃን ሆነ። #ኢሳ. 13፥10፤ ሕዝ. 32፥7፤ ኢዩ. 2፥10፤31፤ 3፥15።
13ከዚህ በኋላ ስመለከት አንድ ንስር በሰማይ መካከል እየበረረ በታላቅ ድምፅ “የቀሩት ሦስቱ መላእክት የእምቢልታቸውን ድምፅ በሚያሰሙበት ጊዜ በምድር ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ወዮላቸው! ወዮላቸው! ወዮላቸው!” እያለ ሲጮኽ ሰማሁ።
Currently Selected:
የዮሐንስ ራእይ 8: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997