YouVersion Logo
Search Icon

ወደ ሮም ሰዎች 13

13
ለመንግሥት ባለሥልጣኖች መታዘዝ እንደሚገባ
1ማንኛውም ሥልጣን የሚገኘው በእግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ሆነና አሁን ያሉትም ባለሥልጣኖች የተሾሙት በእግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ ሰው ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣን መታዘዝ አለበት። 2ስለዚህ ባለሥልጣንን የሚቃወም ሁሉ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይቃወማል፤ የማይታዘዝም ሁሉ በራሱ ላይ የቅጣትን ፍርድ ያመጣል። 3ገዢዎች የሚያስፈሩት ክፉ አድራጊዎችን እንጂ መልካም አድራጊዎችን አይደለም፤ ባለሥልጣንን እንዳትፈራ ትፈልጋለህን? እንግዲያውስ መልካሙን ነገር አድርግ፤ ከእርሱም ምስጋናን ታገኛለህ። 4ባለሥልጣን ለአንተ መልካም እንዲያደርግ የተሾመ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው፤ ባለሥልጣን ሰይፍ የታጠቀው በከንቱ ስላልሆነ ክፉ አድራጊ ከሆንክ ባለሥልጣንን ፍራ፤ እርሱ ክፉ አድራጊዎችን በመቅጣትና የእግዚአብሔርን በቀል በማሳየት እግዚአብሔርን ያገለግላል። 5ስለዚህ ለመንግሥት ባለሥልጣኖች መታዘዝ ይገባችኋል፤ የምትታዘዙትም የእግዚአብሔርን ቊጣ ስለ መፍራታችሁ ብቻ ሳይሆን ኅሊናችሁም ስለሚወቅሳችሁ መሆን አለበት።
6ግብር የምትከፍሉትም ስለዚህ ነው፤ ባለሥልጣኖች በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩት እግዚአብሔርን ለማገልገል ነው። 7እንግዲህ ለበላይ ባለሥልጣን ሊደረግ የሚገባውን ሁሉ አድርጉ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን ክፈሉ፤ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ። #ማቴ. 22፥21፤ ማር. 12፥17፤ ሉቃ. 20፥25።
እርስ በርስ ስለ መፈቃቀር
8የማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፤ ሊኖርባችሁ የሚገባ ዕዳ እርስ በርስ መዋደድ ብቻ ይሁን፤ ሰውን የሚወድ ሕግን ይፈጽማል። 9“አታመንዝር፤ አትግደል፤ አትስረቅ፤ የሌላ ሰው የሆነውን ማናቸውንም ነገር አትመኝ” የሚሉት ትእዛዞችና ሌሎችም ትእዛዞች ሁሉ “ሰውን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” በሚለው በአንዱ ትእዛዝ ተጠቃለው ይገኛሉ። #ዘዳ. 5፥17-19፤21፤ ዘሌ. 19፥18። 10ሰውን የሚወድ ሁሉ በሚወደው ላይ ክፉ ነገር አያደርግበትም፤ ስለዚህ ሰውን የሚወድ ሕግን ሁሉ ይፈጽማል ማለት ነው።
11እንግዲህ ከእንቅልፍ የምትነቁበት ሰዓት አሁን መድረሱን ዕወቁ፤ በፊት ካመንበት ጊዜ ይልቅ አሁን የምንድንበት ቀን ይበልጥ ወደ እኛ ቀርቦአል። 12ሌሊቱ እያለፈ ነው፤ ቀኑም ቀርቦአል፤ ስለዚህ በጨለማ የሚሠራውን ሥራ እንተው፤ የብርሃንን የጦር መሣሪያ እንልበስ። 13ቅጥ ባጣ ፈንጠዝያ፥ በስካር፥ በዝሙትና በመዳራት፥ በጭቅጭቅና በምቀኝነት ሳይሆን በቀን ብርሃን እንደሚኖሩ ሰዎች በጨዋነት እንመላለስ። 14ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት እንጂ የሥጋችሁን ፍላጎት ለማርካት አታስቡ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in