YouVersion Logo
Search Icon

ወደ ሮም ሰዎች 6

6
ከኃጢአት ተለይቶ በክርስቶስ መኖር
1እንግዲህ ምን እንላለን? የእግዚአብሔር ጸጋ እንዲበዛ በኃጢአት ጸንተን እንኑርን? 2አይደለም! እኛ በሞት የመለየትን ያኽል ከኃጢአት የተለየን ሆነን ሳለ እንዴት በኃጢአት ጸንተን እንኖራለን? 3ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ ለመሆን የተጠመቅን ሁሉ የሞቱም ተካፋዮች ለመሆን መጠመቃችንን አታውቁምን? 4በጥምቀት ከእርሱ ጋር በተቀበርን ጊዜ የእርሱም ሞት ተካፋዮች ሆነናል፤ ስለዚህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሞት እንደ ተነሣ እኛም በአዲስ ሕይወት እንኖራለን። #ቆላ. 2፥12።
5በሞቱ ከእርሱ ጋር እንዲህ አንድ ከሆንን እንዲሁ በትንሣኤው ከእርሱ ጋር አንድ እንሆናለን። 6ኃጢአተኛው ሰውነታችን እንዲወገድና የኃጢአት ባሪያዎች መሆናችን እንዲቀር አሮጌው ሰውነታችን ከክርስቶስ ጋር መሰቀሉን እናውቃለን። 7የሞተ ሰው ለኃጢአት ከመገዛት ነጻ ነው። 8እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር በሕይወት እንደምንኖር እናምናለን፤ 9ክርስቶስ ከሞት በመነሣቱ ምክንያት ዳግመኛ እንደማይሞትና ሞትም በእርሱ ላይ ሥልጣን እንደሌለው እናውቃለን። 10እርሱ በሞተ ጊዜ ኃጢአት በእርሱ ላይ ሥልጣን እንዳይኖረው በማያዳግም ሁኔታ አንድ ጊዜ ሞቶአል፤ አሁንም በሕይወት ሲኖር ለእግዚአብሔር ይኖራል። 11እንግዲህ እናንተ የመሞት ያኽል ከኃጢአት እንደ ተለያችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ግን ለእግዚአብሔር በሕይወት እንደምትኖሩ አስቡ።
12ስለዚህ ኃጢአት በሚሞተው ሰውነታችሁ ላይ ሥልጣን እንዲኖረውና ለሥጋ ምኞትም ተገዢ እንዲያደርጋችሁ አትፍቀዱለት። 13እንዲሁም የሰውነታችሁን ክፍሎች የዐመፅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታስገዙ፤ ነገር ግን ከሞት ተነሥታችሁ ሕያዋን እንደ ሆናችሁ በማድረግ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ የሰውነታችሁንም ክፍሎች ሁሉ የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አስገዙ። 14አሁን እናንተ የምትኖሩት ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላልሆነ ኃጢአት ሊገዛችሁ አይገባም።
የጽድቅ አገልጋዮች መሆን
15እንግዲህ ምን እንላለን? ከሕግ በታች መሆናችን ቀርቶ ከጸጋ በታች ስለ ሆንን ኃጢአት እንሥራ ማለት ነውን? ከቶ አይደለም! 16ለአንድ ሰው አገልጋዮች ሆናችሁ ለመታዘዝ ራሳችሁን ስታቀርቡ ለዚያ ለምትታዘዙለት ሰው አገልጋዮች መሆናችሁን ታውቃላችሁ፤ እንዲሁም ለኃጢአት ብትታዘዙ ሞትን ለሚያመጣባችሁ ኃጢአት አገልጋዮች ትሆናላችሁ፤ ለእግዚአብሔር ብትታዘዙ ግን ጽድቅን ታገኛላችሁ። 17እናንተ አስቀድሞ የኃጢአት ባሪያዎች ነበራችሁ፤ አሁን ግን ለተቀበላችሁት ትምህርት ከልብ በመታዘዛችሁ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። 18ከኃጢአት ባርነት ነጻ ወጥታችሁ የጽድቅ አገልጋዮች ሆናችኋል። 19እኔ እንዲህ ለሰው በሚገባ ቋንቋ የምናገረው ከአስተሳሰባችሁ ደካማነት የተነሣ ነው። አስቀድሞ የሰውነት ክፍሎቻችሁን የርኲሰትና የዐመፅ አገልጋዮች አድርጋችሁ እንዳቀረባችሁ ሁሉ እንዲሁም አሁን የሰውነት ክፍሎቻችሁ እንዲቀደሱ የጽድቅ አገልጋዮች አድርጋችሁ አቅርቡ።
20የኃጢአት ባሪያዎች በነበራችሁበት ጊዜ ጽድቅ የማድረግ ግዴታ አይሰማችሁም ነበር። 21ታዲያ፥ በዚያን ጊዜ ምን ጥቅም አገኛችሁ? አሁን ከሚያሳፍራችሁ ነገር በቀር ምንም ጥቅም አላገኛችሁም፤ የዚህም ነገር መጨረሻ ሞት ነው። 22አሁን ግን ከኃጢአት ባርነት ነጻ ወጥታችሁ የእግዚአብሔር አገልጋዮች በመሆናችሁ ቅድስናን ታገኛላችሁ፤ የቅድስናም መጨረሻ የዘለዓለም ሕይወት ነው። 23ከኃጢአት የሚገኘው ዋጋ ሞት ነው፤ ከእግዚአብሔር የሚሰጠው ስጦታ ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት የሚገኘው የዘለዓለም ሕይወት ነው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in