YouVersion Logo
Search Icon

ወደ ሮም ሰዎች 7

7
ከሕግ ነጻ ስለ መሆን
1ወንድሞቼ ሆይ! ይህን አታውቁምን? የምናገረው ሕግን ለሚያውቁ ሰዎች ነው፤ ሕግ በሰው ላይ ሥልጣን የሚኖረው ሰው በሕይወት እስካለ ድረስ ብቻ ነው። 2ለምሳሌ፥ ያገባች ሴት ባልዋ በሕይወት እስካለ ድረስ ከእርሱ ጋር በሕግ የታሰረች ናት፤ ባልዋ ከሞተ ግን ከታሰረችበት ሕግ ነጻ ናት። 3ስለዚህ ባልዋ በሕይወት እያለ ሌላ ወንድ ብታገባ አመንዝራ ትባላለች። ባልዋ ከሞተ ግን ከእርሱ ጋር ከታሰረችበት ሕግ ነጻ ትወጣለች፤ ሌላ ወንድ ብታገባም አመንዝራ አይደለችም። 4ወንድሞቼ ሆይ፥ የእናንተም ሁኔታ እንደዚሁ ነው፤ እናንተ የክርስቶስ አካል ክፍል ስለ ሆናችሁ በሞት የመለየትን ያኽል ከሕግ ተለይታችኋል፤ ስለዚህ ለእግዚአብሔር አገልግሎት ፍሬ እንድናፈራ ከሞት የተነሣው የክርስቶስ ወገኖች ሆናችኋል። 5በሥጋ ፈቃድ እንመላለስ በነበረበት ጊዜ በሕግ የሚነሣሣው ክፉ ምኞት ለሞት ፍሬ እንድናፈራ በሰውነታችን ክፍሎች ውስጥ ይሠራ ነበር። 6አሁን ግን አስሮን ከነበረው ሕግ በሞት የመለየት ያኽል ስለ ተለየን ከሕግ እስራት ነጻ ወጥተናል፤ ስለዚህ ከእንግዲህ የምናገለግለው በአዲሱ መንፈሳዊ መመሪያ እንጂ አስቀድሞ በተጻፈው በአሮጌው የሕግ መመሪያ አይደለም።
ሕግና ኃጢአት
7እንግዲህ ምን እንላለን? ሕግ ራሱ ኃጢአት ነውን? አይደለም! ነገር ግን ኃጢአት ምን መሆኑን እንዳውቅ ያደረገኝ ሕግ ነው። ሕግ “አትመኝ” ባይል ኖሮ ምኞት ምን መሆኑን ባላወቅሁም ነበር። #ዘፀ. 20፥17፤ ዘዳ. 5፥21። 8ኃጢአት ከሕግ በመጣው ትእዛዝ ዕድል አግኝቶ ምኞትን ሁሉ በኔ ውስጥ እንዲቀሰቀስ አደረገ። ሕግ ከሌለ ግን ኃጢአት የሞተ ነገር ነው። 9ቀድሞ ሕግ ባልነበረበት ጊዜ እኔ በሕይወት እኖር ነበር፤ የሕግ ትእዛዝ በመጣ ጊዜ ግን እኔ ሞቼ ኃጢአት ሕይወት አገኘ። 10ለሕይወትም የተሰጠው የሕግ ትእዛዝ በእኔ ላይ ሞትን አመጣብኝ። 11ኃጢአት የሕግን ትእዛዝ ሰበብ አድርጎ አታለለኝ፤ በትእዛዝም አማካይነት ገደለኝ። #ዘፍ. 3፥13።
12ስለዚህ ሕግ ቅዱስ ነው፤ ትእዛዝም ቅዱስና እውነት መልካምም ነው። 13ታዲያ፥ ይህ መልካም የሆነው ነገር በእኔ ሞትን አመጣብኝ ማለት ነውን? አይደለም! ነገር ግን ኃጢአት፥ ኃጢአት ሆኖ እንዲገለጥ በመልካሙ ነገር አማካይነት ሞትን አመጣብኝ፤ ስለዚህ ኃጢአት በትእዛዝ አማካይነት የበለጠ ኃጢአተኛ ሆነ።
በሰው ሕይወት ውስጥ ያለ ትግል
14ሕግ መንፈሳዊ መሆኑን እናውቃለን። እኔ ግን የኃጢአት ባሪያ ለመሆን የተሸጥሁ ሥጋዊ ነኝ። 15እኔ የማደርገውን አላውቅም፤ የምወደውን ነገር ማድረግ ትቼ የምጠላውን ነገር አደርጋለሁ። #ገላ. 5፥17። 16እንግዲህ እኔ የማደርገው የማልፈልገውን ነገር ከሆነ ሕግ መልካም እንደ ሆነ እመሰክራለሁ። 17ማድረግ የማልፈልገውን ነገር የሚያደርገው በእኔ ውስጥ ያለው ኃጢአት ነው እንጂ እኔ አይደለሁም። 18በእኔ ወይም በእኔ ሥጋዊ ባሕርይ ምንም መልካም ነገር እንደሌለ ዐውቃለሁ፤ መልካም ነገርን የማድረግ ፍላጎት ቢኖረኝም እንኳ ያን መልካም ነገር ለማድረግ ችሎታ የለኝም። 19ማድረግ የምፈልገውን መልካም ነገርን አላደርግም፤ ዳሩ ግን የማልፈልገውን ክፉ ነገር አደርጋለሁ። 20ማድረግ የማልፈልገውን ክፉ ነገር የማደርግ ከሆንኩ ይህን የሚያደርገው በእኔ ውስጥ ያለው ኃጢአት ነው እንጂ እኔ አይደለሁም ማለት ነው።
21ስለዚህ ሕግ በሥራ ላይ ውሎ አያለሁ፤ መልካም ነገርን ማድረግ ስፈልግ ክፉ ነገርን ለማድረግ እገደዳለሁ። 22ውስጣዊ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል። 23ይሁን እንጂ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር እየተቃረነ በሰውነቴ ክፍሎች ውስጥ ለሚሠራው የኃጢአት ሕግ እስረኛ የሚያደርገኝ ሌላ የተፈጥሮ ዝንባሌ በሰውነቴ ክፍሎች ውስጥ መኖሩን አያለሁ። 24እኔ ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ! ከዚህ ሟች ሰውነትስ ማን ያድነኛል? 25በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለሚያድነኝ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን!
እንግዲህ እኔ በአእምሮዬ፥ ለእግዚአብሔር ሕግ ተገዢ ስሆን በሥጋ ባሕርዬ ለኃጢአት ሕግ ተገዢ ሆኜአለሁ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in