1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13
13
ስለ ፍቅር
1በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር፥ ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሿሿ ጸናጽል ነኝ። 2#ማቴ. 17፥20፤ 21፥21፤ ማር. 11፥23።ትንቢት የመናገር ስጦታ ቢኖረኝ፥ ምስጢርን ሁሉ ባውቅ፥ ዕውቀትን ሁሉ ብረዳ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። 3ያለኝን ሁሉ ለድኾች ባካፍል፥ ሰውነቴንም እንዲቃጠል ለእሳት አሳልፌ ብሰጥ፥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም።
4ፍቅር ይታገሳል፤ ቸርነትንም ያደርጋል። ፍቅር አይቀናም፤ አይመካም፤ አይታበይም፤ 5ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም፤ ራስ ወዳድ አይደለም፤ አይበሳጭም፥ በደልን አይቆጥርም። 6ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ በዐመፅ ደስ አይሰኝም። 7ፍቅር ሁሉን ይታገሣል፤ ሁሉን ያምናል፤ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፤ በሁሉ ነገር ይጸናል።
8ፍቅር ከቶ አይወድቅም፤ ትንቢት የመናገር ስጦታም ቢሆን ይሻራል፤ ልሳንም ቢሆን ይቀራል፤ ዕውቀትም ቢሆን ያልፋል። 9ምክንያቱም የምናውቀው በከፊል ነው፤ ትንቢት የምንናገረውም በከፊል ነው። 10ነገር ግን ፍጹም የሆነው ሲመጣ በከፊል የነበረው ይሻራል። 11ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፤ እንደ ልጅ አስብ ነበር፤ እንደ ልጅም አሰላስል ነበር። ሙሉ ሰው በሆንኩ ጊዜ ግን የልጅነትን ጠባይ ትቻለሁ። 12አሁን የምናየው በመስተዋት ውስጥ እንደሚታይ በድንግዝግዝ ነው፤ በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን። አሁን የማውቀው በከፊል ነው፤ በዚያን ጊዜ እኔ ራሴ ሙሉ በሙሉ የታወቅሁትን ያህል ዐውቃለሁ። 13እንግዲህ እምነት፥ ተስፋ፥ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።
Currently Selected:
1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in