YouVersion Logo
Search Icon

1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4

4
የሐዋርያት አገልግሎት
1እንግዲህ ሰው እኛን እንደ ክርስቶስ አገልጋዮችና እንደ እግዚአብሔር ምሥጢራት መጋቢዎች ይቁጠረን። 2ከዚህም በላይ፥ በመጋቢዎች ዘንድ የታመነ ሆኖ መገኘት ያሻል። 3ነገር ግን በእናንተ ዘንድ ወይም በማንም ሰው ዘንድ ቢፈረድብኝ ለእኔ ምንም አይደለም፤ እኔም በራሴ እንኳ አልፈርድም፤ 4#ጥበ. 17፥11።በራሴ ላይ ከኅሊናዬ ምንም የለም፤ ነገር ግን በዚህ አልጸድቅም፤ በእኔ ላይ የሚፈርድ ግን ጌታ ነው። 5ስለዚህም፥ በጨለማ የተሰወረውን ወደ ብርሃን የሚያወጣ ደግሞም የልብን ምክር የሚገልጥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ፥ ጊዜው ሳይደርስ አንዳች አትፍረዱ፤ በዚያን ጊዜም እያንዳንዱ ምስጋናው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይሆናል።
6ወንድሞች ሆይ! ስለ አንዱ በሌላው ላይ አንዳችሁም እንዳትታበዩ “ከተጻፈው አትለፍ፤” የሚለውን በእኛ እንድትማሩ፥ በዚህ ስለ እናንተ ስል ራሴንና አጵሎስን እንደ ምሳሌ ተናገርሁ። 7አንተን እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልከውስ ምን አለህ? እንግዲህ የተቀበልክ ከሆንክ፥ እንዳልተቀበልክ የምትመካው ስለ ምንድነው?
8አሁንማ ሞልቶላችኋል! አሁንማ ሀብታሞች ሆናችኋል! ያለ እኛ ነግሣችኋል! እኛም ከእናንተ ጋር እንድንነግሥ፥ በእርግጥ ብትነግሡ ኖሮ፥ መልካም በሆነ! 9እግዚአብሔር እኛን ሐዋርያቱን ሞት እንደ ተፈረደባቸው ሰዎች ከሁሉ ይልቅ የኋለኞች እንዳደረገን ይመስለኛል፤ ምክንያቱም ለዓለም ለመላእክትም ለሰዎችም ትንግርት ሆነናል። 10እኛ ስለ ክርስቶስ ሞኞች ነን፤ እናንተ ግን በክርስቶስ ልባሞች ናችሁ፤ እኛ ደካሞች ነን፤ እናንተ ግን ብርቱዎች ናችሁ፤ እናንተ የተከበራችሁ ናችሁ፤ እኛ ግን የተዋረድን ነን። 11እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፥ እንጠማለንም፤ እንራቆታለን፥ እንጐሰማለንም፥ እንዲሁም እንንከራተታለን፤ 12#የሐዋ. 18፥3።በገዛ እጃችን እየሠራን እንደክማለን፤ ሲረግሙን እንመርቃለን፤ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፤ 13ክፉ ሲናገሩን በትሕትና እንመልስላቸዋለን፤ እስከ አሁን ድረስ የዚህ ዓለም ጥራጊ የሁሉም ጉድፍ ሆነናል።
14እንደምወዳችሁ ልጆቼ አድርጌ ልገሥጻችሁ እንጂ ላሳፍራችሁ ይህን አልጽፍም። 15በክርስቶስ አእላፍ መሪዎች ቢኖሩአችሁ ብዙ አባቶች የሉአችሁም፤ እኔ በክርስቶስ ኢየሱስ በወንጌል ወልጄአችኋለሁና። 16#1ቆሮ. 11፥1፤ ፊልጵ. 3፥17።እንግዲህ “እኔን የምትመስሉ ሁኑ፤” ብዬ እለምናችኋለሁ። 17በዚህ ምክንያት የተወደደውንና የታመነውን በጌታ ልጄ የሆነውን ጢሞቴዎስን ልኬላችኋለሁ፤ በየስፍራው በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እኔ እንደማስተምረው በክርስቶስ ኢየሱስ የሆነው መንገዴን እርሱ ያሳስባችኋል። 18አንዳንዶች ግን ወደ እናንተ የማልመጣ እየመሰላቸው የታበዩ አሉ፤ 19ነገር ግን ጌታ ቢፈቅድ ፈጥኜ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ የትዕቢተኞችንም ኃይል አውቃለሁ እንጂ ቃላቸውን አይደለም፤ 20የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ነው እንጂ በቃል አይደለምና። 21ምን ትፈልጋላችሁ? በትር ይዤ ወደ እናንተ እንድመጣ? ወይስ በፍቅርና በየውሃት መንፈስ?

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in