1ኛ የዮሐንስ መልእክት 3
3
1 #
ዮሐ. 1፥12። የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን እንድንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ፤ እንዲሁም ነን። ዓለም እርሱን ስላላወቀው እኛንም አያውቀንም። 2ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፥ ምን እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ቢገለጥ ግን እርሱን እንደምንመስል እናውቃለን፥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና። 3በእርሱ ይህ ተስፋ ያለው ሁሉ እርሱ ንጹሕ እንደሆነ ራሱን ያነጻል።
4ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ ዓመፅን ያደርጋል፥ ኃጢአት ደግሞ ዓመጽ ነው። 5#ዮሐ. 1፥29።ኃጢአትን ሊያስወግድ እንደ ተገለጠ ታውቃላችሁ፥ በእርሱም ኃጢአት የለም። 6በእርሱ የሚኖር ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፤ ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ አላየውም፥ አላወቀውምም። 7ልጆች ሆይ፥ ማንም አያስታችሁ፥ እርሱ ጻድቅ እንደሆነ ጽድቅን የሚያደርግ ጻድቅ ነው። 8ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ምክንያቱም ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ጀምሮ ኃጢአትን ይሠራል። የእግዚአብሔር ልጅ የተገለጠውም የዲያብሎስን ሥራ ለማፍረስ ነው። 9ዘሩ በእርሱ ስለሚኖር ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፤ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደ ኃጢአትን ሊያደርግ አይችልም። 10የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ ይገለጣሉ፤ ጽድቅን የማያደርግ ሁሉ እና ወንድሙን የማይወድ ከእግዚአብሔር አይደለም።
11 #
ዮሐ. 13፥34። ከመጀመሪያ የሰማችሁት መልእክት ይህ ነውና፥ እርሱም፦ እርስ በርሳችን እንዋደድ፥ 12#ዘፍ. 4፥8።ከክፉው እንደነበረው ወንድሙንም እንደ ገደለው እንደ ቃየል አይደለም፤ ስለምንስ ገደለው? የእርሱ ሥራ ክፉ፥ የወንድሙ ግን ጽድቅ ስለ ነበረ ነው። 13ወንድሞች ሆይ፥ ዓለም ቢጠላችሁ አትደነቁ። 14#ዮሐ. 5፥24።እኛ ወንድሞቻችንን ስለምንወድ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ፍቅር የሌለው በሞት ይኖራል። 15ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ ገዳይ የሆነም ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት በእርሱ እንደማይኖር ታውቃላችሁ። 16እርሱ ስለ እኛ ሕይወቱን አሳልፎ ስለ ሰጠን በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ሕይወታችንን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባናል። 17ነገር ግን ማንም የዚህ ዓለም ሀብት ቢኖረው፥ ወንድሙም ተቸግሮ አይቶ ባይራራለት፥ የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴት ይኖራል? 18ልጆቼ ሆይ፥ በሥራ እና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ።
19በዚህም ከእውነት መሆናችንን እናውቃለን፥ በፊቱም ልባችንን እናሳርፋለን፥ 20ልባችን ቢወቅሰን እንኳ እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል። 21ወዳጆች ሆይ፥ ልባችን የማይወቅሰን ከሆነ በእግዚአብሔር ዘንድ ድፍረት አለን፤ 22ትእዛዛቱን ስለምንጠብቅ፥ በፊቱም ደስ የሚያሰኘውን ስለምናደርግ፥ የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እናገኛለን። 23#ዮሐ. 13፥34፤ 15፥12፤17።ትእዛዚቱም ይህች ናት፥ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥም እንድናምንና፥ እርሱም እንዳዘዘን እርስ በርሳችን እንድንዋደድ ነው። 24ትእዛዙን የሚጠብቅ ሁሉ በእርሱ ይኖራል እርሱም ይኖርበታል፤ በእኛ እንደሚኖር በዚህ እናውቃለን፥ ይኸውም በሰጠን በመንፈሱ ነው።
Currently Selected:
1ኛ የዮሐንስ መልእክት 3: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in