YouVersion Logo
Search Icon

1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2

2
ሕያው ድንጋይና የተመረጠ ሕዝብ
1እንግዲህ ክፋትን ሁሉ፥ ተንኰልን ሁሉ፥ ግብዝነትን፥ ቅንዓትን ሐሜትን ሁሉ አስወግዱ። 2ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ፥ አዲስ እንደ ተወለዱ ሕፃናት ንጹሑን መንፈሳዊ ወተት ተመኙ፤ 3#መዝ. 34፥8።እነሆ፥ ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችኋልና።
4በሰው ዘንድ ወደ ተናቀው፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠውና ክቡር ወደ ሆነው ወደዚህ ሕያው ድንጋይ እየቀረባችሁ፥ 5እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ለማቅረብ፥ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ፥ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ። 6#ኢሳ. 28፥16።ምክንያቱም በመጽሐፍ
“እነሆ፥ የተመረጠና ክቡር የማእዘን ድንጋይ፥ በጽዮን አኖራለሁ፤
በእርሱም የሚያምን አያፍርም፤”
ተብሎ ተጽፎአልና። 7#መዝ. 118፥22።እንግዲህ ለእናንተ ለምታምኑት ይህ ድንጋይ ክቡር ነው፤ ለማያምኑት ግን
“ግንበኞች የናቁት ድንጋይ
እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ።”
8 # ኢሳ. 8፥14፤15። ደግሞም፦
“ሰዎችን የሚያሰናክል ድንጋይ
የሚጥላቸውም ዓለት ሆነ፤”
የሚሰናከሉት ቃሉን ባለመታዘዛቸው ነው፤ አስቀድመውም ለዚህ የተመደቡ ናቸው።
9 # ዘፀ. 19፥5፤6፤ ኢሳ. 43፥20፤ ዘፀ. 19፥5፤ ዘዳ. 4፥20፤ 7፥6፤ 14፥2፤ ቲቶ 2፥14፤ ኢሳ. 43፥21፤ ኢሳ. 9፥2። እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን አስደናቂ ሥራ እንድታውጁ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ እግዚአብሔር ለራሱ ያደረጋችሁ ቅዱስ ሕዝብ ናችሁ። 10#ሆሴዕ 2፥23።ቀድሞ የእርሱ ወገን አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የእግዚአብሔር ወገን ናችሁ፤ ቀድሞ ምሕረትን አላገኛችሁም ነበር፤ አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል።
እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች መኖር
11ወዳጆች ሆይ! ባዕዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ 12ምናልባት “ክፉ አድራጊዎች ናቸው” ብለው ቢያሙአችሁም እንኳ እግዚአብሔር በሚጎበኝበት ቀን፥ ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ እርሱን እንድያከብሩት በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን።
13ስለ ጌታ ብላችሁ ሥልጣን ለተሰጣቸው ሰዎች ሁሉ፥ ንጉሥም ቢሆን ከሁሉ በላይ እንደመሆኑ ታዘዙ። 14ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት በጎም የሚያደርጉትን ለማመስገን ከእርሱ ተልከዋልና ለአገረ ገዢዎችም ቢሆን ታዘዙ። 15በዚህ መንገድ መልካም በማድረግ የሞኞችን አላዋቂነት ዝም እንድታሰኙ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። 16እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ሆናችሁ በነጻነት ኑሩ እንጂ ነጻነታችሁን የክፋት መሸፈኛ አታድርጉት። 17ሰውን ሁሉ አክብሩ፤ ወንድሞችን ውደዱ፤ እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ንጉሥን አክብሩ።
የክርስቶስ መከራ ምሳሌነት
18እናንተ አገልጋዮች ሆይ! ለደጎችና ለገሮች ጌቶቻችሁ ብቻ ሳይሆን ለክፉዎችም በፍጹም አክብሮት ታዘዙ። 19ስለ እግዚአብሔር ብሎ በግፍ መከራን ሲቀበል የሚታገሥ ምስጋና ይገባዋል። 20ክፉ ሥራ ሠርታችሁ ቅጣት ስትቀበሉ ብትታገሡ ምን ምስጋና ይኖራችኋል? ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሡ፥ ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ያስገኝላችኋል። 21ለዚህ ተጠርታችኋል፤ ምክንያቱም ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን አርአያነት እንድትከተሉ ምሳሌን ሊተውላችሁ ነው። 22#ኢሳ. 53፥9።እርሱ ኃጢአት አላደረገም፤ በአፉም ተንኰል አልተገኘበትም፤ 23#ኢሳ. 53፥7።ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፤ መከራንም ሲቀበል አልዛተም፤ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ 24#ኢሳ. 53፥5፤6።ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በመስቀል ላይ ተሸከመ፤ በእርሱ ቁስል እናንተ ተፈውሳችኋል። 25እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበር፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in