2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 9
9
በኢየሩሳሌም ለሚገኙ ክርስቲያኖች የተደረገ መዋጮ
1ለቅዱሳን ስለሚደረገው አገልግሎት ልጽፍላችሁ አያስፈልግም። 2በጎ ፈቃዳችሁን ስለማውቅ፤ በእናንተ ላይ የምመካበትን ምክንያት ለመቄዶንያ ሰዎች፥ “አካይያ ከአምና ጀምሮ ተዘጋጅቶአል፤” ብዬ ተናግሬለሁ፤ ቅንዐታችሁም ብዙዎችን አነሣሥቶአል። 3ነገር ግን ለእነርሱ እንደተናገርኩት፥ ስለ እናንተ ያለን ትምክህት እንዲሁ በባዶ እንዳልሆነ ለማረጋገጥ ወንድሞችን እልካለሁ፤ 4ምናልባት የመቄዶንያ ሰዎች ከእኔ ጋር ቢመጡና ሳትዘጋጁ ቢያገኟችሁ፥ ያን ያህል ማለታችን እንድታፍሩ ባይሆንም፥ እንዲህ በመመካታችን ግን እንድናፍር ያደርገናል። 5እንግዲህ ዝግጁ እንድትሆኑ ወንድሞች አስቀድመው ወደ እናንተ መጥተው፥ አስቀድማችሁ ተስፋ የሰጣችሁትን የልግስና ስጦታ እንደ ግዴታ ሳይሆን በበጎ ፈቃደኝነት ቀደም ብለው እንዲያዘጋጁ፥ እነርሱን መለመን አስፈላጊ መሆኑን አስቤበታለሁ።
6ይህን አስታውሱ፤ በጥቂት የዘራ ጥቂት ያጭዳል፤ ብዙ የዘራም ብዙ ያጭዳል። 7#ሲራ. 20፥10-15።እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና፥ እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበው ይስጥ፤ በኀዘን ወይም በግድ ግን አይሁን። 8ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን አግኝታችሁ በበጎ ሥራ በቸርነት እንድትለግሱ፥ እግዚአብሔር ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል። 9ይህም፥
#
መዝ. 112፥9። “በተነ፤ ለድኾችም ሰጠ፤
ጽድቁ ለዘለዓለም ይኖራል፤”
ተብሎ ተጽፏል። 10#ኢሳ. 55፥10።ለዘሪ ዘርን፥ ለመብላትም እንጀራን የሚሰጥ፥ እርሱ የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል፤ ያበረክትላችሁማል፤ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤ 11በእኛ በኩል እግዚአብሔርን የማመስገኛ ምክንያት የሚሆነውን ልግስናችሁ በሁሉ ነገር ባለ ጠጎች ያደርጋችኋል። 12የዚህ አገልግሎት ረድኤት ለቅዱሳን የሚጎድላቸውን በሙሉ የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ብዙ ምስጋና ምክንያትም ነው። 13በዚህ አገልግሎት ስለ ተፈተናችሁ፥ በክርስቶስ ወንጌል በማመናችሁ ስለ ታዘዛችሁ፥ እነርሱንና ሁሉንም ስለምትረዱበት ልግስና፥ እግዚአብሔርን ያከብራሉ፤ 14እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ታላቅ ጸጋ የተነሣ ስለ እናንተም በሚጸልዩበት ጊዜ ይናፍቁአችኋል። 15ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን።
Currently Selected:
2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 9: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in