2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10
10
ጳውሎስ ስለ አገልግሎቱ የሰጠው መከላከያ
1እኔም ጳውሎስ፥ ፊት ለፊት ሳገኛችሁ ትሑት የሆንሁ፥ ከእናንተ ርቄ ግን ደፋር የምሆንባችሁ፥ በክርስቶስ የዋህነትና ገርነት እመክራችኋለሁ፤ 2ስመጣ ግን በዓለማዊ ልማድ እንደምንመላለስ በሚቆጥሩን በአንዳንዶች ላይ በድፍረት ለመናገር አስባለሁ፤ እናንተን ግን በዚያ ድፍረት እንድናገር እንዳታደርጉኝ እለምናችኋለሁ። 3ምንም እንኳ በሥጋ የምንመላለስ ብንሆን፥ ውጊያችንን ግን እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ 4ምክንያቱም የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለም፤ ምሽግን ለመስበር መለኮታዊ ኃይል አለው። 5በእግዚአብሔር እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ክርክርና ማንኛውም የእብሪት እንቅፋት እናፈርሳለን፤ አእምሮን ሁሉ እየማረክን ለክርስቶስ እንዲታዘዝ እናደርጋለን፤ 6መታዘዛችሁም በተፈጸመች ጊዜ አለመታዘዝን ሁሉ ልንበቀል ተዘጋጅተናል።
7በፊታችሁ ያለውን ተመልከቱ። ማንም የክርስቶስ መሆኑን ተረድቶ ከሆነ፥ እርሱ የክርስቶስ እንደሆነ እኛም የክርስቶስ መሆናችንን እንዳይዘነጋ። 8በሥልጣናችን ከበፊቱ ይልቅ አሁን ብመካም እንኳን፥ ይህን ጌታ የሰጠን እናንተን ለማነጽ እንጂ እናንተን ለማፍረስ ስላልሆነ አላፍርበትም። 9በመልእክቶቼ የማስፈራራችሁ እንዳይመስላችሁ። 10አንዳንዶች “መልእክቶቹ ከባድና ጠንካራ ናቸው፤ ሰውነቱ ሲታይ ግን ደካማ ነው፤ ንግግሩም የተናቀ ነው፤” ይላሉ። 11እንዲህ የሚሉን፥ በርቀት ሆነን በመልእክታችን የምንናገረውን በአካልም ስንገኝ የምናደርገው መሆኑን፥ ይወቁት። 12ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን መቁጠር ወይም ራሳችንን ማስተያየት አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ እርስ በራሳቸው ሲያመዛዝኑ፥ እርስ በራሳቸውም ሲተያዩ፥ አስተዋይ አይደሉም።
13እኛ ግን፥ እግዚአብሔር እንደ ወሰነልን፥ እስከ እናንተ በሚደርስ ወሰን እንጂ፥ ያለ ልክ አንመካም። 14ወደ እናንተ እንደማንደርስ አድርገን ከመጠን አናልፍምና፤ የክርስቶስን ወንጌል በመስበክ እስከ እናንተ ድረስ መጥተናል፥ እናንተን በማካለል እንዳለፍናችሁ በማሰብ ወሰን አናልፍም። 15በሌሎች ድካም ያለ ልክ አንመካም፤ ነገር ግን እምነታችሁ ሲያድግ፥ የምንሠራበት ወሰን እየሰፋ ይሄዳል፤ 16በሌላው ክፍል ስለ ተሠራው ነገር መመካት ሳያስፈልገን፥ ከእናንተ አልፎ ባለው አገር ወንጌልን ለማብሰር ያስችለናል። 17#ኤር. 9፥24።“የሚመካ በጌታ ይመካ፤” 18ምክንያቱም እግዚአብሔር የሚያመሰግነው እንጂ፥ ራሱን የሚያመሰግን እርሱ ተፈትኖ የሚወጣ አይደለም።
Currently Selected:
2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in