ወደ ቈላስይስ ሰዎች 1
1
ሰላምታ
1በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ ወንድማችንም ጢሞቴዎስ፥ 2በቈላስይስ ለሚኖሩ ቅዱሳንና በክርስቶስ ለታመኑ ወንድሞች፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ጸጋና ሰላም ይሁን።
ጳውሎስ ስለ ቈላስይስ ሰዎች ለእግዚአብሔር ያቀረበው ምስጋና
3ስለ እናንተ ስንጸልይ፥ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን ሁልጊዜ እናመሰግናለን፤ 4ምክንያቱም በክርስቶስ ኢየሱስ ያላችሁን እምነትና ለቅዱሳንም ሁሉ ያላችሁን ፍቅር ስለ ሰማን ነው፤ 5ይህም እምነትና ፍቅር በሰማይ በተዘጋጀላችሁ ተስፋ ላይ የተመሠረተ ነውና፤ ስለዚህም ተስፋ የእውነት ቃል በሆነው በወንጌል አስቀድማችሁ ሰማችሁ። 6ይህም ወንጌል ወደ እናንተ ደርሶአል፤ የእግዚአብሔርንም ጸጋ በእውነት ከሰማችሁበትና ካወቃችሁበት ቀን ጀምሮ፥ በእናንተ መካከል እንደ ሆነው እንዲሁ በመላው ዓለም ፍሬ ያፈራል፤ ያድጋልም። 7#ቈላ. 4፥12፤ ፊልሞ. 1፥23።ይህንንም ከተወደደ ከእኛም ጋር አብሮ ባርያ ከሆነው ከኤጳፍራ ተማራችሁ፤ እርሱም ስለ እናንተ ታማኝ የክርስቶስ አገልጋይ ነው። 8ደግሞም በመንፈስ ስለ ሆነው ስለ ፍቅራችሁ አስታወቀን።
9ስለዚህ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምረን በመንፈሳዊ ጥበብና ማስተዋል ሁሉ የፈቃዱን እውቀት እንድትሞሉ እየለመንን፥ ስለ እናንተ ጸሎትን አልተውንም፤ 10በዚህም በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁና በእግዚአብሔር እውቀት እያደጋችሁ፥ ለጌታ እንደሚገባው ፍጹም ደስ የሚያሰኘውን ሕይወት እንድትኖሩ ነው። 11እንደ ክብሩ ኃያልነት በሁሉ ኃይል እንድትበረቱና ሁሉንም ነገር በትዕግሥት በጽኑ ለመወጣት እንድትዘጋጁ እንዲሁም ደስ በመሰኘት 12በብርሃን የቅዱሳንን ርስት እንድንካፈል ያበቃንን አብን እንድታመሰግኑት ነው። 13እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፤ ወደ ተወደደውም ልጁ መንግሥት አፈለሰን፤ 14#ኤፌ. 1፥7።በእርሱም ተዋጅተን የኃጢአትን ስርየት አገኘን።
የክርስቶስ ልዕልና
15 #
ጥበ. 7፥26። እርሱም ለማይታየው አምላክ ምሳሌ ነው፤ የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው፤ 16የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤ 17እርሱም ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም ነገር በእርሱ አብሮ ተዋቅሮአል። 18#ኤፌ. 1፥22፤23።እርሱም አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ እርሱ በሁሉ ነገር ቀዳሚ በመሆን መጀመሪያ ነው፤ ከሙታንም በኩር ነው። 19እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ በማደሩ ተደስቷል፤ 20#ኤፌ. 2፥16።በመስቀሉም ደም ሰላምን በማድረግ በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን ነገሮች ሁሉ በእርሱ አማካይነት ከራሱ ጋር አስታርቋል።
21እናንተም ከእርሱ ተለይታችሁና ክፉ በመሥራት በሐሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን 22አሁን በእርሱ ፊት ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ቅዱሳን አድርጎ ለማቅረብ በሥጋዊው አካሉ በሞቱ አስታረቃችሁ። 23ይህም የሚሆነው ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ ከሰማችሁትም ከወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ በእምነት የምትጸኑ ከሆነ ነው፤ ይህም ወንጌል ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ የተሰበከ ነው፤ እኔም ጳውሎስ የእርሱ አገልጋይ ሆንሁ።
የጳውሎስ ሐዋርያዊ አገልግሎት
24አሁን በመከራዬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ አካሉም ስለ ሆነችው ስለ ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስ ካለፈባቸው መከራዎች መካከል የጐደሉትን በሥጋዬ እፈጽማለሁ። 25ስለ እናንተ እንደተሰጠኝ እንደ እግዚአብሔር መጋቢነት፥ የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽሜ እንድሰብክ እኔ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆንሁ፤ 26ይህም ቃል ከዘመናትና ከትውልዶች ጀምሮ ተሰውሮ የነበረ ምሥጢር ነው፤ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል፤ 27ለእነርሱም እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያለው የዚህ ምሥጢር ክብር ባለጠግነት ምን እንደሆነ ሊያሳውቅ ወደደ፤ ምሥጢሩም የክብር ተስፋ የሆነው በእናንተ ያለው ክርስቶስ ነው። 28እኛም በክርስቶስ ፍጹም አድርገን ሁሉንም ሰው ለማቅረብ ሁሉንም ሰው እየገሠጽንና ሁሉንም ሰው በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው፤ 29ለዚህም ነገር ደግሞ፥ በእኔ ውስጥ በኃይል በሚያቀጣጥለው ጉልበት ሁሉ እየተጋደልሁ እደክማለሁ።
Currently Selected:
ወደ ቈላስይስ ሰዎች 1: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in