YouVersion Logo
Search Icon

ወደ ቈላስይስ ሰዎች መግቢያ

መግቢያ
ይህ መልእክት የተጻፈው በታናሽቱ እስያ ከኤፌሶን በስተ ምሥራቅ በምትገኘው በቆላስይስ ከተማ ላለችው ቤተ ክርስቲያን ነው። ይህች ቤተ ክርስቲያን የተቋቋመችው በጳውሎስ አልነበረም። ቢሆንም በሮም ሥር የእስያ ዋና ከተማ ከሆነችው ከኤፌሶን ቅዱስ ጳውሎስ የወንጌል መልእክተኞችን ወደ ቈላስይስ ያሰማራ ነበር። በቈላስይስ ቤተ ክርስቲያን “እግዚአብሔርን ለማወቅና የተሟላ መዳንን ለማግኘት እያንዳንዱ ሰው ለመንፈሳዊ ኀይሎችና ሥልጣኖች መስገድ አለበት” የሚሉ ሐሰተኞች መምህራን መኖራቸውን ጳውሎስ ሰምቶ ነበር። በተጨማሪም እነዚህ መምህራን “እያንዳንዱ ሰው እንደ ግዝረት ያሉ ሥርዓቶች፥ እንዲሁም የምግብንና ሌሎችን የአይሁድ ትእዛዛት መጠበቅ አለበት” ይሉ ነበር።
ጳውሎስ ይህን መልእክት የጻፈው እውነተኛውን የክርስትና መልእክት በማቅረብ የእነርሱን ሐሰተኛ ትምህርት ለመቃወም ነበር። ካቀረባቸውም መልሶች ዋነኛው “ኢየሱስ ክርስቶስ የተሟላ መዳንን ይሰጣል፤ እነኚ ሌሎቹ ተግባሮች ግን መሠረታዊ የመዳን አንቀጾች አይደሉም” የሚለው ነው። እግዚአብሔር በክርስቶስ ዓለምን ፈጠረ፤ በእርሱም በኩል ወደ ራሱ መልሶ ያመጣዋል፤ ዓለም የመዳን ተስፋ የሚኖረው ክርስቶስን ከልብ በማመን ብቻ ነው፤ በዚህ መሠረት ጳውሎስ ይህ ታላቅ ትምህርት በአማኞች ሕይወት እንዴት ሊተረጐም እንደሚችል ያስረዳል።
ይህን መልእክት ከጳውሎስ ተቀብሎ ወደ ቈላስይስ ሊያደርስ ከተላከው ከቲኪቆስ ጋር አብሮ የነበረው ኦኔሲሞስ እንደ ነበረ መመልከት ጠቃሚ ነው፤ ጳውሎስ ስለዚህ ኦኔሲሞስ ስለ ተባለው አገልጋይ አንሥቶ ለፊልሞና ሌላ መልእክት ጽፎአል።
አጠቃላይ የመጽሐፉ ይዘት
መግቢያ (1፥1-8)
የክርስቶስ ባሕርይና ሥራ (1፥9—2፥19)
በክርስቶስ አዲስ ሕይወት (2፥20—4፥6)
ማጠቃለያ (4፥7-18)
ምዕራፍ

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in