YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ኢሳይያስ 40

40
የመዳን የተስፋ ቃል
1አጽናኑ፥ ሕዝቤን አጽናኑ ይላል አምላካችሁ። 2ለኢየሩሳሌም ልብ ተናገሩ፤ የተቀጠረችበት ወራት እንደ ተፈጸመ፥ ኃጢአትዋም እንደ ተሰረየ፥ ከጌታም እጅ ስለ ኃጢአትዋ ሁሉ ሁለት እጥፍ እንደ ተቀበለች ወደ እርሷ ጩኹ። 3#ሲራ. 48፥10፤ ባሮክ 5፥7፤ ማቴ. 3፥3፤ ማር. 1፥3፤ ዮሐ. 1፥23።#ሉቃ. 3፥4-6።የአዋጅ ነጋሪ ቃል፦ “የጌታን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጎዳና በበረሀ አስተካክሉ። 4ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፥ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ጠማማውም ይቃናል፥ ስርጓጉጡም ሜዳ ይሆናል፤ 5ከዚያም የጌታ ክብር ይገለጣል፥ ሥጋ ለባሹም ሁሉ በአንድነት ያየዋል፥ የጌታ አፍ ይህን ተናግሮአል።”
6 # ያዕ. 1፥10-11፤ 1ጴጥ. 1፥24-25። አንድ ድምጽ “ጩኽ!” አለኝ፤ “ምን ብዬ ልጩኽ?” አልኩ። ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሣር ነው፥ ክብሩም ሁሉ እንደ ምድረ በዳ አበባ ነው። 7የጌታ እስትንፋስ ይነፍስበታል፤ ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፤ በእውነት ሕዝቡ ሣር ነው። 8ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፥ የአምላካችን ቃል ግን ለዘለዓለም ጸንታ ትኖራለች። 9የምሥራች የምትነግሪ ጽዮን ሆይ፥ ከፍ ወደለው ተራራ ውጪ፤ የምሥራች የምትነግሪ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ድምፅሽን በኃይል አንሺ፤ አንሺ፥ አትፍሪ፤ ለይሁዳም ከተሞች፦ እነሆ፥ አምላካችሁ! ብለሽ ንገሪ። 10#ኢሳ. 62፥11፤ ራእ. 22፥12።እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ኃያል ይመጣል ክንዱም ስለ እርሱ ይገዛል፤ እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር ደመወዙም በፊቱ ነው። 11#ሕዝ. 34፥15፤ ዮሐ. 10፥11።መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፥ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፥ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል። 12ውኆችን በእፍኙ የሰፈረ፥ ሰማይንም በስንዝር የለካ፥ የምድርንም አፈር በመስፈሪያ ሰብስቦ የያዘ፥ ተራሮችን በሚዛን ኮረብቶችንም በሚዛኖች የመዘነ ማን ነው? 13#ሮሜ 11፥34፤ 1ቆሮ. 2፥16።የጌታን መንፈስ ያዘዘ፥ ወይስ አማካሪ ሆኖ ያስተማረው ማን ነው? 14ወይስ ከማን ጋር ተመካከረ? ወይስ ማን መከረው? የፍትህንም መንገድ ማን አስተማረው? እውቀትንስ ማን አስተማረው? የማስተዋልንስ መንገድ ማን አሳየው? 15#ጥበ. 11፥22፤ ሲራ. 10፥16፤17።እነሆ፥ አሕዛብ በገንቦ እንዳለች ጠብታ ናቸው፥ በሚዛንም እንዳለ ትንሽ ትቢያ ተቈጥረዋል፤ እነሆ፥ ደሴቶችን እንደ ቀላል ነገር ያነሣል። 16ሊባኖስ ለማንደጃ እንስሶችዋም ለሚቃጠል መሥዋዕት አይበቁም። 17አሕዛብ ሁሉ በፊቱ እንዳልነበሩ ናቸው፤ ከምንም እንደሚያንሱ፥ እንደ ባዶ ነገር ይቈጠራሉ። 18#የሐዋ. 17፥29።እንግዲህ እግዚአብሔርን በማን ትመስሉታላችሁ? ወይስ በምን ምሳሌ ታስተያዩታላችሁ? 19የተቀረጸውንስ ምስል ሠራተኛ ሠርቶታል፥ አንጥረኛም በወርቅ ለብጦታል፥ የብሩንም ሰንሰለት ቅርጽ እንዲሰጥ አፍስሶለታል። 20#ጥበ. 13፥11-19።ለዚህ መባዕ ገንዘቡ ያልበቃው ድሀ የማይነቅዘውን እንጨት ይመርጣል፤ ምስሉም እንዳይናወጥ ያቆመው ዘንድ ብልህ ሠራተኛን ይፈልጋል።
21አላወቃችሁም? ወይስ አልሰማችሁ ይሆን? ከጥንትስ አልተወራላችሁም? ወይስ ምድር ከተመሠረተች ጀምሮ አላስተዋላችሁም? 22እርሱ በምድር ክበብ ላይ ይቀምጣል፥ በእርሷም የሚኖሩት እንደ አንበጣ ናቸው፤ ሰማያትን እንደ መጋረጃ የሚዘረጋቸው እንደ ድንኳንም ለመኖርያ የሚዘረጋቸው፥ 23መስፍኖችንም እንዳልነበሩ፥ የምድርንም ፈራጆች እንደ ከንቱ ነገር የሚያደርጋቸው እርሱ ነው። 24ገና እንደ ተተከሉና እንደ ተዘሩ፥ በምድርም ሥር ገና እንደ ሰደዱ ወዲያውኑ ነፈሰባቸው፥ እነርሱም ደረቁ፥ ዐውሎ ነፋስም እንደ እብቅ ጠረጋቸው። 25እንግዲህ የሚስተካከለኝ ማን አለ? ከማንስ ጋር አመሳሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ። 26#ባሮክ 3፥34-35።ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቍጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፥ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛትና በክህሎቱ ብርታት አንድ እንኳ አይጎለውም። 27ያዕቆብ ሆይ፥ እስራኤል ሆይ፦ “መንገዴ ከጌታ ተሰውራለች፥ ፍርዴም በአምላኬ ቸል ተብላለች” ለምን ትላለህ? ለምንስ እንዲህ ትናገራለህ? 28አላወቅህም? አልሰማህም? ጌታ የዘለዓለም አምላክ ነው፤ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፤ አይታክትም፤ ማስተዋሉም አይመረመርም። 29ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፤ ጉልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል። 30ብላቴኖች ይደክማሉ፥ ይታክታሉም፤ ጐበዛትም ፈጽሞ ይወድቃሉ። 31ጌታን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፤ አይደክሙም።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Video for ትንቢተ ኢሳይያስ 40