YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ኢሳይያስ 43

43
የመታደስና የጥበቃ ተስፋ
1አሁንም ያዕቆብ ሆይ፥ የፈጠረህ፥ እስራኤልም ሆይ፥ የሠራህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህም ጠርቼሃለሁ፥ አንተ የእኔ ነህ። 2በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰምጡህም፤ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፤ ነበልባሉም አይፈጅህም። 3እኔ የእስራኤል ቅዱስ አምላክህ ጌታ መድኃኒትህ ነኝ፤ ግብጽን ለአንተ ቤዛ አድርጌ፥ ኢትዮጵያንና ሳባንም ለአንተ ፋንታ እሰጣለሁ። 4በዓይኔ ፊት የከበርህና የተመሰገንህ ነህና፥ እኔም ወድጄሃለሁና ስለዚህ ሰዎችን ለአንተ፥ አሕዛብንም ለነፍስህ እሰጣለሁ። 5እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ ዘርህንም ከምሥራቅ አመጣዋለሁ፥ ከምዕራብም እሰበስብሃለሁ። 6ሰሜንን፦ “መልሰህ አምጣ፥” ደቡብንም፦ “ልቀቅ፥ ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፥ አምጣ እለዋለሁ፤ 7በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ።” 8ዐይኖች ያሏቸውን ዕውር ሕዝቦችን፥ ጆሮዎችም ያሏቸውን ደንቆሮቹን አውጣ! 9አሕዛብ ሁሉ በአንድነት ይሰብሰቡ፥ ወገኖችም ይከማቹ፤ ከመካከላቸው ይህን የሚናገር፥ የቀድሞውንስ ነገር የሚያሳየን ማን ነው? እንዲጸድቁ ምስክሮቻቸውን ያምጡ፥ ሰምተውም፦ “እውነት ነው” ይበሉ። 10ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ እኔም እንደሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ፥ እናንተ የመረጥሁትም አገልጋዬ ምስክሮቼ ናችሁ ይላል ጌታ፤ ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም ከእኔም በኋላ አይኖርም። 11እኔ፥ እኔ ጌታ ነኝ፥ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም። 12ተናግሬአለሁ፥ አድኛለሁ፥ አሳይቻለሁ፥ በእናንተም ዘንድ ባዕድ አምላክ አልነበረም፤ ስለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ፥ ይላል ጌታ። 13እኔም አምላክ ነኝ፥ ከጥንት ጀምሮ እኔ ነኝ ከእጄም የሚያመልጥ የለም፤ እሠራለሁ፥ የሚከለክልስ ማን ነው? 14የእስራኤል ቅዱስ፥ የሚቤዣችሁ፥ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ስለ እናንተ ወደ ባቢሎን ሰድጃለሁ፥ ከላዳውያንንም ሁሉ ስደተኞች አድርጌ በሚመኩባቸው መርከቦች አዋርዳቸዋለሁ። 15ቅዱሳችሁ፥ የእስራኤል ፈጣሪ፥ ንጉሣችሁ፥ ጌታ እኔ ነኝ። 16ጌታ እንዲህ ይላል፥ በባሕር ውስጥ መንገድን በኃይለኛም ውኃ ውስጥ መተላለፊያን ያደርጋል፤ 17ሠረገላውንና ፈረሱን ሠራዊቱንና አርበኛውን ያወጣል፥ እነርሱ ግን በአንድነት ተኝተዋል፥ አይነሡም፤ ቀርተዋል፥ እንደ ጥዋፍ ኩስታሪም ጠፍተዋል። 18የፊተኛውን ነገር አታስታውሱ፥ የጥንቱንም ነገር አታስቡ። 19እነሆ፥ አዲስ ነገርን አደርጋለሁ፤ እርሱም አሁን ይበቅላል፥ ይህን እናንተም አታውቁም? በምድረ በዳም መንገድን በበረሃም ወንዞችን እዘረጋለሁ። 20የምድረ በዳ አራዊት፤ ቀበሮዎችና ሰጎኖች ያከብሩኛል፤ ለመረጥሁት ሕዝቤ ውሃ ላጠጣ፥ በምድረ በዳ ውሃ፤ በበረሓም ምንጭ እሰጣለሁ። 21ለራሴ ያበጀሁት ሕዝብ ምስጋናዬን እንዲያውጅ ይህን አደርጋለሁ። 22ያዕቆብ ሆይ፥ አንተ ግን አልጠራኸኝም፥ አንተም እስራኤል ሆይ፥ በእኔ ዘንድ ደክመሃል። 23ለሚቃጠል መሥዋዕት በጎችህን አላቀረብህልኝም፤ በሌላም መሥዋዕትህ አላከበርኸኝም፤ በእህልም ቁርባን አላስቸገርሁህም፤ በዕጣንም አላደከምሁህም። 24ዕጣንም በገንዘብ አልገዛህልኝም፤ በመሥዋዕትህም ስብ አላጠገብኸኝም፤ ነገር ግን በኃጢአትህ አስቸገርከኝ፥ በበደልህም አደከምከኝ። 25መተላለፍህን፦ ስለ እኔ ስል የምደመስስ እኔ ነኝ፤ ኃጢአትህንም አላስብም። 26አሳስበኝ፥ በአንድነትም ሆነን እንፋረድ፤ እንድትጸድቅ ነገርህን ተናገር። 27ፊተኛው አባትህ ኃጢአት ሠርቶአል፥ መምህሮችህም በድለውኛል። 28ስለዚህ የመቅደሱን አለቆች አረከስኩ፥ ያዕቆብንም እርግማን፥ እስራኤልንም ስድብ አደረግሁ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Video for ትንቢተ ኢሳይያስ 43