YouVersion Logo
Search Icon

ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 1

1
ሰላምታ
1 # የሐዋ. 16፥12። የኢየሱስ ክርስቶስ ባርያዎች የሆኑ ጳውሎስና ጢሞቴዎስ፥ በፊልጵስዩስ ለሚኖሩ ከኤጲስ ቆጶሳትና ከዲያቆናት ጋር በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት ቅዱሳን ሁሉ፤
2ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
የጳውሎስ ጸሎት ለፊልጵስዩስ ሰዎች
3እናንተን ባሰብኋችሁ ጊዜ ሁሉ አምላኬን አመሰግነዋለሁ፤ 4ሁልጊዜ በጸሎቴ ሁሉ ስለ ሁላችሁም በደስታ እጸልያለሁ፤ 5ምክንያቱም ከመጀመሪያዋ ቀን አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ወንጌልን በመስበክ አብራችሁ ስለ ሠራችሁ ነው። 6በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እርሱ እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንደሚፈጽመው በዚህ እርግጠኛ ሆኛለሁ፤ 7በእስራቴም ወንጌልንም መመከቻና መጽኛ በማድረግ ሁላችሁ ከእኔ ጋር በጸጋ ተካፋዮች ስለ ሆናችሁ፥ በልቤ ትኖራላችሁና ስለ ሁላችሁ ይህን ላስብ ይገባኛል። 8በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሁላችሁንም ምን ያኽል እንደምናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነውና። 9ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ እጸልያለሁ፤ 10እንዲህም ያለው እውቀት የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ እንድትወድዱ ስለሚረዳችሁ ነው፤ በዚህም ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ንጹሖችና ያለ ነቀፋ በመሆን 11ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ከኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኝ የጽድቅ ፍሬ የተሞላችሁ እንድትሆኑ ነው።
ለጳውሎስ ሕይወቱ ክርስቶስ እንደሆነ
12ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! ይህ የደረሰብኝ በእውነት ወንጌልን ለማስፋፋት እንደሆነ እንድታውቁ እወዳለሁ። 13#የሐዋ. 28፥30።ስለዚህም እስራቴ ስለ ክርስቶስ እንደሆነ በክብር ዘበኞች ሁሉና በሌሎች ሁሉ ዘንድ ተገልጦአል፤ 14በጌታ ካሉት ወንድሞች የሚበዙት በእስራቴ ላይ ጽኑ መተማመን ኖሩዋቸው የእግዚአብሔርን ቃል ለመናገር ያለ ፍርሃት ከፊት ይልቅ ደፍረዋል።
15በእርግጥ አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብካሉ፤ 16እነዚህ የኋለኞቹ ወንጌልን ለመመከት እንደ ተሾምሁ አውቀው በፍቅር ይሰብካሉ፤ 17እነዚያ የፊተኞቹ ግን በእስራቴ ላይ መከራን የሚያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ያለ ንጹሕ ልቦና ከራስ ወዳድነት በመነሣት ስለ ክርስቶስ ያወራሉ። 18ዳሩ ግን ይህ አድራጎታቸው ግድ የሚል ምን ነገር አለው? ብቻ በማመካኘትም ሆነ በእውነት በሁሉ መንገድ ክርስቶስ ይሰበክ እንጂ፤ ስለ ሆነም እኔ በዚህ ደስ ብሎኛል። ወደፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል፤ 19ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ እርዳታ አማካይነት ለመዳኔ እንደሚሆንልኝ አውቄያለሁና፤ 20ይህ ናፍቆቴ ተስፋዬም ነውና፤ በምንም ዓይነት ነገር አላፍርም፤ ነገር ግን በሕይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ እንደ ወትሮው እንዲሁ አሁንም በሥጋዬ ይከብራል ብዬ በሙሉ ድፍረት እናገራለሁ። 21ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና። 22ነገር ግን በሥጋ መኖር ማለት ለእኔ ፍሬያማ ሥራ የምሠራበት ቢሆን፥ ምን እንደምመርጥ አላውቅም። 23በእነዚህም በሁለቱ አማራጮች መካከል እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፤ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤ 24ነገር ግን ስለ እናንተ በሥጋ መኖሬ ይበልጥ አስፈላጊ ነገር ነው። 25ይህንንም ተረድቼ፥ በእምነት እንድታድጉና ደስ እንዲላችሁ ከእናንተ ከሁላችሁም ጋር እንደምቈይና እንደምኖር አውቃለሁ፤ 26በዚህም በእናንተ ዘንድ እንደገና ስለ መገኘቴ፥ በክርስቶስ ኢየሱስ መመካታችሁ በእኔ እንዲበዛላችሁ ነው።
27ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ብቻ ኑሩ፤ በዚህም መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል እምነት አብራችሁ መጋደላችሁንና በአንድ መንፈስ ጸንታችሁ መቆማችሁን እሰማለሁ። 28በምንም ዓይነት ነገር በተቃዋሚዎቻችሁ አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፤ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤ 29ስለ ሆነም በክርስቶስ የምታምኑ ብቻ ሳትሆኑ ስለ እርሱ መከራንም ደግሞ የምትቀበሉ ትሆናላችሁ፤ ይህም ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ 30#የሐዋ. 16፥19-40።በእኔ ያያችሁት አሁንም በእኔ እንደሆነ የምትሰሙት፥ ያው መጋደል ደርሶባችኋልና።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in